6ተኛ ሳምንት ትውስታ

ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ የበቀለበት ተራራ ሲሆን፣ በዚህ ቦታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ምልክቱ የነገረበት ስለሆነ ስያሜውን ያገኘው ከዚህ ነው (ማቴ 24፡3) ቤተ ክርስቲያንም ለምእመናን የዘመኑን መቅረብ ከምልክቶቹ ጋር በማነጻጸር ታስተምርበታለች፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ስለ ሐሳዊ መሲህ መምጣት፤ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በስሙ እንደሚነሡ፣ (ማቴ 24፡5)፣ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመኑ እንደሚመጡ (1ኛ ዮሐ 4፡3፣ 2ኛ ዮሐ 2፡18)፣ የዓመጽ ሰው እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በሐሰተኛ ድንቆችና ምልክቶች እያታለለ በቤተ መቅደስ እንደሚቀመጥ (2ኛ ተሰ 2፡3-4) ፣ የጥፋት ሥራዎች እንደሚታዩ፤ ማለትም ሰዎች ገንዘብን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ እንደሚሆኑ (2ኛ ጢሞ 3፡1-7) እና የመሳሰሉ ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ የተናገረውን ቤተ ክርስቲያን ደግማ ታስታውሰናለች፡፡
በመጨረሻም ”ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።” (መዝ 49/50/፡2-3) በተባለው መሠረት ለፍርድ እንደሚመጣ የምናስታውስበት ሳምንት ደብረ ዘይት ተብሎ በየዓመቱ ይታወሳል፡፡
ለሁላችንም ቃለ ሕይወትን አሰምቶ ወደ መንግሥቱ ያስገባን
