መጻጉዕ

የ4ኛው ሳምንት ትውስታ

መጻጉዕ ማለት ድውይ፣ ሕሙም በሽተኛ ማለት ሲኾን፣ በዚህ ሳምንት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱን

ይታወስበታል፡፡  መነሻ ታሪክ አድርገን የምናስታውሰው የሠላሳ ስምንት ዓመቱን በሽተኛ ቢኾንም (ዮሐ 5፡5-10) ከእርሱ ጋር የተፈወሱትን ሁሉ ይታወሱና የጌታ አዳኝነት በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን (ማቴ 8፡1-4)፣ ዕውር ማብራቱን (ዮሐ 9፡1-11)፣ አንካሶችን ማርታቱን (ማቴ 12፡13)፣ ልምሾዎችን ማዳኑን (ሐዋ 14፡10፣ አጋንንትን ማውጣቱን (ማር 9፡25)፣ … ለመሳሰሉት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ በማድረግ “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል” (መዝ 40፡3) በማለት ምን ያህል ፈጣሪ ለሕሙማን ረዳታቸው እንደሆነ እየተነሣ ይነገርበታል፣ ይታወስበታል፡፡

እግዚአብሔር በደዌ ያሉትንም ይፈውስልን፣

እኛንም በደዌ ሥጋ ወነፍስ ከመያዝ ይጠብቀን፡፡

መንፈሳዊ የሕይወት ምክር

  • አንድ ወጣኒ መናኝ አንድን ታላቅ አባት ጥሩ ሰው የሚባለው ምን የሚያደርግ ነው ብሎ ቢጠይቃቸው፤ እኚህ ትልቅ አባትም መልሰው ዘወትር ለኃጢአቱ የሚጨነቅና ይቅርታ የሚጠይቅ፤ ዘወትር በሥራና በትጋት የተጠመደ፤ ከመናገር ዝምታን ገንዘብ የሚያደርግ፤ ትእዛዛቱን የሚጠብቅና እራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው በማለት መለሱለት፡፡
    • ዓሣ ከውኃ ወጥቶ ከቆየ ወዲያው እንደሚሞት ክርስቲያንም ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ከወጣ እንደዚሁ ይሞታል፡፡ ዓሣው ቶሎ ተምልሶ ወደ ውኃው ሲገባ እንደሚድን ሰውም በንስሐ ቶሎ ሲመለስ እግዚአብሔር የይቅርታውን በር ይከፍትለታል፤ ስለዚህ ንስሐን እንደ ቀላል ነገር አትቁጠረው፤
    • ከተሰወረ ፍቅር የተገለጠ ዘለፋ፣ ከጠላት መልካም ሐሳብ የወዳጅ ክፉ ምክር፣ ከራቀ ወንድም የቀረበ ወዳጅ ሳይሻል እንደማይቀር አትዘንጋ፤
    • መልካም ሞት የመልካም ኑሮ ውጤት ነው፤
    • ሳያልፍ የመጣ ክፉ ነገር የለምና እስኪያልፍ ታገሥ፤
    • አንደበተ ትልቅ ውስጠ ቀላል እንዳትሆን ተጠንቀቅ
    • በእግዚአብሔር እንጂ በደጋፊዎች አትተማመን በደጋፊዎች ከተማመንክ ከሰባራ ወንበር ላይ እንደተቀመጥክ ቁጠረው፤
    • የሰይጣን ደህና ባይኖረውም፣ ብቻውን ካለ ሰይጣን ይልቅ በሰው ላይ ባደረ ሰይጣን ተጠንቀቅ፣ በሰው ላይ ያደረ ሰይጣን በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስትለው ከሰውየው ጋር ተጣብቆ ያስቸግራልና፡፡
    • ሰዎች በአንተ ላይ ምንም እንዳያወሩ ሥልጣን የለህምና፤ የሚሉህን እየሰማህ ስህተትህን አስተካክል፤

ምንጭ፡- (አባ ሳሙኤል አዲሱ፣ መንፈሳዊ የሕይወት ምክር፣ ታሕሣሥ 2005 ዓ.ም፣ አ.አ.፣ ዕሌኒ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ86-89)

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top