የ3ኛው ሳምንት ትውስታ
ምኵራብ የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ በዚህ በጸሎት ቦታ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነበባሉ፣ ትምህርትም ይሰጥባቸዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቦታው ይገኝ እንደነበር ወንጌል “በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ” (ማር 1፡21) ይላል፡፡
እርሱ አስቀድሞ በነቢያት “ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትንም አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፥ እኔም እመሰገናለሁ” (ሐጌ 1፡8) እንዳለ እንዲሁ በመመለኪያው ቦታ እጅግ ቅድስናን እንደሚያድል፣ በረከትን፣ ትምህርትን፣ ፈውስን እንደሚሰጥ የሚያመለክት ነው፡፡
ወንጌል በተደጋጋሚ “ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ” በማለት በቤተ ጸሎት መገኘት መንፈሳዊ ልምዳችን እንዲኾን በተግባር ያሳየን (ሉቃ 4፡16፣ ማር1:21)፡፡ ይህም ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በዓል ለማክበር በዚያ ይገኝ የነበረው ፈለጉን እንድንከተለው ነው “ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንደአስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ” እንዲል (ሉቃ 2፡42)
ከዚህ ምእመናን ወደ ቤተ ለጸሎት ዘወትር ስለመገኘት እንድናውቅና እንድናስብ ይገባ ዘንድ ከጾሙ ሳምንታት ውስጥ አንዱን ምኵራብ በሚል ስያሜ ተሰይሞ እንድናስበው ተደረገ (ማቴ.21፥13)፡፡ ስለዚህ ምዕመናን በዚህ የጸሎት ስፍራ በቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር እየተገኘን እንድንጸልይ፣ እንድንማርና ሕይወታችንን በዚያ እንድንመሠረት የእግዚአብሔር ቃል “በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ” (ነህምያ 6፡10) ይለናል፡፡
እግዚአብሔር በቤቱ ተክሎ ያኑረን፡፡

