ጾም ማለት ከእግዚአብሔር የታዘዘ እውነተኛ ሕግ ነው፡፡ ነገር ግን የሥራውን ፍሬ መጀመሪያ እንገልጻለን ጾም ማለት መጀመሪያ ዓይናችን ክፉ ነገርን እንዳያይ፤ ጆሮአችን ክፉ ነገርን እንዳይሰማ፤ አንደበታችን ክፉ እንዳይናገር መከልከል ነው እንጂ እንዲያው ሥጋና ቅቤን ብቻ መተው አይደለም፡፡
መቼም የሰው ባሕርይ በዚህ ዓለም ሲኖር ሁል ጊዜ በደስታና በተድላ ለመኖር ነው የሚጥረው፤ ይኸውም ለሰው ልጅ ሐሳብ ሁለት መንገድ አለው፤ አንዱ በሕግ የተፈቀደ፤ ሁለተኛው በሕግ ያልተፈቀደ ነው፡፡ በሕግ ያልተፈቀደ ማለት እግዚአብሔርንና ሰውን የሚበድልበት የዓመጽና የኃጢአት ጎዳና ነው፡፡ አባታችን አዳም ከሕግ የወጣ መንገድ ያልታዘዘውን ሥራ ሠርቶ በልቶ ከገነት ወጥቶ ወደ ግዞት እንደሄደ ያመለክተናል፡፡ በሕግ የታዘዘ መንገድ ማለት ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ሀብታምም ቢሆን ወይም ድሃ፤ ያንኑ የመጀመሪያ ዕድሉ የሰጠውን ሀብት በምስጋና ተቀብሎ ፈጣሪውን እያመሰገነ በጾምና በጸሎት፤ ወይም በሐዘንና በደስታም ቢሆን እግዚአብሔርንና ወንድሙን ባይበድልና ሳያስቀይም ‹‹ላብህን ከግንባርህ ጠርገህ እንጀራህን ብላ›› (ዘፍ3፡19) እንደተባለው ሕግን ቢፈጽም፤ እስከ ዘለዓለም የሕይወቱ ምንጭ ሳይደፈን ይኖራል፡፡
ዛሬ ግን ሰዎች ጾምና ጸሎትን <<እግዚአብሔር የማይፈቅደው ሕግ ነው፤ እግዚአብሔር የሚወደውና የታዘዘው ሕግ ያገኙትን ሁሉ ሳይጸየፉ መብላትና በደስታ መኖር ነው>> ብለው በሆቴል ሜዳ ያገኙትን እንደ ጨፌ ሣር የለመለመ መብልና መጠጥ እየተመገቡ እናያለን፡፡ ነገር ገን ይህ እግዚአብሔር የሚወደው ሕግ ይሆን? በእውነት እግዚአብሔር የሚወደው ሰው አጭር ጊዜ በኾነ ሕይወቱ በዚህ ዓለም ላይ ሲኖር ለእርሱ ሲል የተሰቀለለትንና የሞተለትን ፈጣሪው ሁል ጊዜ እያሰበ በጾምና በጸሎት በሐዘንና በትዕግሥት ኾኖ ወደ ፈጣሪው ዓይነ ሕሊናውን ሰቅሎ፤ ዘለዓለማዊ የኾነውን ብርሃናዊ ሕይወት ተጎናጽፎ መኖር ነው፡፡ በዚህ ዓለም ተድላና ሕይወት ለእኛ ነውና የተፈጠረው ብለው ሲፈነጥዙ፤ ቢኖሩ፣ ‹‹ሞት ሲመጣ ጥሩ ቄስ፤ ጦር ሲመጣ ግዙ ፈረስ›› የተባለው ተረት በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፡፡
እኛ ከኃጢአት ቁስል የምንድንበትና የምንፈወስበት በጾምና በጸሎት መኾኑን አንዘንጋ፤ ያለ ጾምና ያለ ሐዘን ደስታ (ሮሜ 5፡3-4)፤ ያለ ሥራም መክበርና ባለጠጋ መኾን አይገኝም፤ ያለዚህ ግን ደስታና ክብረት ቢገኝም እንኳ፤ እውነተኛ ክብረት እውነተኛ ደስታ ሊባል አይገባውም የሌብነት ክብረት ነው እንጂ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የስህተት ትምህርት እያስተማሩ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያቆራርጥን የሚያጣላ ስሕተት የመላበት ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ተነሥተዋል፤ እነ መምህር ሆድ አምላኩ የሚያስተምሩት ቃል ይህን ነው፡- ‹‹ሰውን የሚያረክሰው የበላው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም›› (ማቴ 15፡11) የተባለው ንባብ ዛሬ በኹሉ ዘንድ የተጠና ኾኖአል፡፡ ነገር ግን ይህን ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ ከዐሥርቱ ቃላት ወይም ከስድስቱ ቃላት እንደ ሕግ አድርጎ አልተናገረውም፡፡ ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትህ እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና ሕጋችንን ይተላለፋሉ ብለው በጠየቁት ጊዜ ለነዚያ መልስ ሲሰጥ ሳይታጠቡ ቢበሉ እነሱን ነው የሚጎዳ እንጂ ሰውየውን ወይም የነርሱ እድፍ ሌላኛውን ያገኘውን ሰው አያረክሰውም ሰውን የሚያረክሰው ክፉ ንግግር ነው ብሎ ያስተማረውን ስለ ጾም በማስመሰል ሁሉ ብሉ ብሎናል እያሉ ያስተምራሉ (ፊልጵ 3፡19)፡፡
ወንድሜ ሆይ አባታችንን አዳምን አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ያሳሰረው ማን ነው? አትብላ የተባለውን በመብላቱ አይደለምን? አዳም በመብል ምክንያት ያመጣውን ጠላት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጾም ድል እንደነሣው አታውቅምን? እወቅ፡፡
ሐተታ ሳይበዛ ባጭሩ፣ እንዲያው ነቢያት ካህናት ኹልጊዜ ጠላታቸውን ድል የሚያደርጉት በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪ የሚመለሱበት መሆኑን አትርሳ፤ (ኢዩ 2፡12-15፣ ኤፌ 6፡18፣ ኤርም 36፡7-8) ሆድ አምላኩ ሆይ እባክህ ልብ አድርገህ አስተውል ለአራዊትና ለአንስሳት እንኳን ምግባቸው ልዩነት አለው ለእንስሳ ገለባ፣ ለበሬ ሥጋ ቢያቀርቡለት አይበላም፡፡ ክርስቲያንም በጾም ወራትና በፍስክ ወራት ለይቶ መብላት እንደሚገባው አይዘንጋ ኹል ጊዜ ለሆዴ ማለት አምላኬ አዛዤ እርሱ ነው ያሰኛልና (ሮሜ 16፡18)፡፡
በሐዋርያት ቃል የጸደቀው (ሐዋ 13፡1-3፣ ሲያያዝ የመጣውን የቅዱሳን አበውን እምነትና ትምህርት ጎዳና አድርገን በዚያው መጓዝ ነው እንጂ ወንጌል ባልሄደበት ጎዳና ገሥግሦ የነቢያትን ትንቢት ጥሶ ምሳሌ አፍርሶ የአእምሮን መዝጊያ ሰብሮ የሚያስተምረውን የሚናገረውን መምህር መስማት በገዛ ራሳችን ላይ የኃጢአት መርዝ መነስነስ ነው፡፡
ምንጭ፡- (አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ፣ መርሐ ልቡና፣ መጋቢት 24/1943 ዓ.ም፣ አ.አ. ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ 35-39)
