ቅድስት

የ2ኛው ሳምንት ትውስታ

በሁለተኛው ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም የሚጀምርበት ዋዜማ ስለኾነ እርሱ የጾመው ጾም ቅድስት ጾም መኾኑን የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ ቅድስት ማለት የተለየች ማለት ነውና፡፡ ዐቢይ ጾም መባሉም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ልዩ እና ታላቅ የኾነው አምላካችን ጾሙን ጾሞ፣ እንድንጾም ፍለጋውን የተወልን በመኾኑ  በአጠቃላይ ክርስቲያን ኹሉ በአዋጁ ጾም በቤተ ክርስቲያን በመገኘት፣ ቅዳሴ በማስቀደስ፣ በንስሐ ታጥበን፣ የተዘጋጀን ኹሉ ጸአዳ (ነጭ ልብስ) በመልበስና ሥጋ ወደሙን እየተቀበልን እንጾመዋለን፡፡ ስለዚህም ቅድስት ብለን ሳምንቱን እናሳልፋለን፡፡

በቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ያዜመው ዜማ ቀለም “ዛቲ ዕለት ቅድስት ይዕቲ (ይህች ቀን የተቀደሰች ናት)” ብሎ ይጀምራል፡፡ በዚህ ሳምንት የጾሙን ቅድስና ብቻ ሳይኾን ቅድስና ያላቸውን ሁሉ እናዘክርበታለን፡፡ ሰባኪያንም በሳምንቱ የእግዚአብሔርን ቅድስና (ዘሌ 19፡2)፣  የአማኞቹን ቅድስና (1ኛ ጴጥ 1፡15፣ 1ኛ ተሰ 4፡6)፣ የሰንበትን ቅድስና…ወዘተ (ዘፍ 2፡3፣ ዘጸ 20፡8) ሊያስተምሩበት ይችላሉ፡፡

ቅድስናን ስንሰብክ ቅዱሳን የኾኑትን እያስታወስን ነው፡፡ ለምሳሌ መላእክት  (ማር (ማር 8፡38)፣ ምእመናን በክርስቶስ ደም ቅዱሳን እንደኾኑ (ሮሜ 5፡9) የሃይማኖትን ቅድስና (ይሁዳ 1፡20) እንዴት በሕይወታችንና በኑሮአችን ሁሉ ቅዱሳን መኾን እንዳለብን (2ኛ ጴጥ 3፡11) ከዚህ ዓለም አልፈን ስንሄድ “ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች” መኾን እንደምንችል ለመወያየት “ቅድስት” በሚል ስያሜ ሳምንቱን ሰይመን፤ ስለ ጾም ቅድስና፣ ስለ ሰንበት ቅድስና በአጠቃላይ በዓለም እየኖሩ ከዓለም በቅድስና ስለ መለየት ከወንጌል እየጠቀስን እንማርበታለን (ዮሐ 15:19, ዮሐ 17:6-16፣ 2፡15-16፣ 1ኛ ዮሐ 4፡5)፡፡

የቅድስት ጾም የጌታ በረከት ከኹላችን ጋር ይሁን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top