6ተኛ ሳምንት ትውስታ
የቃሉ ትርጉም ገብር ሥራ፣ ሠራተኛ፣ አገልጋይ ማለት ሲሆን፤ ሔር ደግሞ ቸር፣ መልካም፣ ታማኝ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በሳምንቱ ውስጥ የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ሁሉ ታማኝ አገልጋይ መሆንን ስለሚያመለክት ገብር ሔር በማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ ይሰበክበታል፡፡ ይህን ስብከት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ማቴ 25፡14-25)፡፡
በዚህ ሳምንት ባለሥልጣን እና ዳኛው በሥልጣናቸው ሙስና እንዳይሠሩ፣ ሐኪሙ፣ ነጋዴው፣ ተማሪው፣ ወታደሩ፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛው ሁሉ ስለ ታማኝነት ጥቅም ከቤተ ክርስቲያን ይማራሉ (ቲቶ 2፡9-10፣ ማቴ 23፡23)፡፡ ጳጳሱ፣ ቄሱ፣ ዲያቆኑ፣ ሰባኪውና፣ መምህራኑ ሁሉ በሚያገለግሉት ግልጋሎት ታማኝና ንቁ ሆነው እንዲያገለግሉ ስለ ታማኝነት የሚሰበክበት ሳምንት “ገብር ሔር” ተሰኝቷል (1ኛ ጢሞ 1፡12፣ ሐዋ 26፡16፣ ሮሜ 15፡16፣ ኤፌ 6፡21)፡፡
የሐዋርያው ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ኤጳፍራ የሚባለው “ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ” እንደተባለ (ቆላስ 1፡7)፣ አገልጋይም ቸልተኝነት ካለበት ርግማን እንደሚከተለው በማስጠንቀቅ (ኤር 48፡10) ራሳን አድኖ ሌሎችን የሚያድንበትን የትጋት አገልግሎት እንዲወጣና ሰዎችን ወደ መዳን እንዲያመጣ 30፤ 60፤ 100 ያመረ ፍሬ እያፈራ ለሌላው አርኣያ እንዲሆን ሁሉም በአለበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ “አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ” የሚለውን አምላካዊ ቃል እንዲሰማ የሚሰበክበት ሳምንት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን “ገብር ሔር” ብሎን
መንግሥቱን እንዲያወርሰን ጸጋውን ያድለን፡፡
