“ቃል ሥጋ ሆነ”

ቃል ሥጋ ሆነ(ዮሐ. ፩፥፲፬/114)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

እንኳን ለጌታችን፣ ለአምላካችን እና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችኁ

ይህ ቃል ሥጋ የመኾን ምስጢር፡- እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለዱ (ሰው በመሆኑ) [አምላክ ሰው የሆነበት] ልዩ ምስጢር፣ የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት ከመጣበት ሞት የዳነበት ምስጢር፣ ቤተ ክርስቲያናችን “ተዋሕዶ” የሚለውን ስያሜ ያገኘችበት፣ እኛም “ክርስቲያን” የተባልንበት ምስጢር፣ ሰማያዊው “ነገረ እግዚአብሔር” ለሰው ልጅ የተገለጠበት ምስጢር ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ ታላቅነት ሲናገር “የተነገረውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባህርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ፣ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፤ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 634) ፡፡

ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም፣ የእግዚአብሔር አብ ልጅ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፡፡

የመጀመሪያው (ቀዳማዊው) ልደት ዘመን ከመቆጠሩ፣ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት፣ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ልዩ በሆነ ምስጢር (አካል  ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ) የተወለደው ልደት ነው፡፡ (መዝ. 27 1013 ምሳ. 825)፡፡

ሁለተኛው ደኃራዊ ልደቱ፣ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ በኋላ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋው ሥጋ፣ ከነፍሷ በነፍስ ነሥቶ፣ ያለ አባት በፍጹም ተዋሕዶ የተወለደው ልደት ነው፡፡ (ገላ. 44 ኢሳ. 714 ኢሳ. 96)፡፡

ቅዱስ ናጣሊስ “ከድንግል በተወለደው በደኃራዊ ልደቱ፣ የሰው ልጅ ሆነ፡፡ እርሱ አንዱ በመለኮት ከአብ ጋር አንድ የሚሆን የሚተካከል ፍጹም አምላክ ነው፡፡ እርሱ ብቻ ከድንግል በተወለደው ልደት፣ በሥጋ ከሰው ጋር አንድ የሚሆን ፍጹም ሰው ነው” ሲል አስተምሮናል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ናጣሊስ
46፥3-4)፡፡

አምላክ ለምን ሰው ሆነ?

አምላክ ሰው የሆነበትን ምስጢር በሙሉ መርምሮ የሚያውቅ ባይኖርም፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እና  በሊቃውንት አስተምህሮ በተተነተነው (በተገለጠው) መሠረት፣ “አምላክ ሰው የሆነበት፤ ሰውም አምላክ የሆነበት ምስጢር ነው ስንል

. አርአያ ለመሆን” (ዘፍ. 312 መዝ. 614)

. ቤዛ ለመሆን” (ኢሳ. 644)

. ፍቅሩን ለመግለጽ” (ሆሴ. 144)

. አምላክ መሆኑን ለመግለጽ” (ሮሜ 1፥19-20፤ ዮሐ. 3፥16)

. የሰይጣንን ጥበብ ለመሻር” (ዕብ. 2፥9/14-15) እና በመሳሰሉት አምላክ በረቂቅ
የተዋሕዶ ምስጢር በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ አምላክ በተለየ አካሉ
ሰው ሆኗል፡፡

በሃይማኖተ አበው መጽሐፋችን ምዕራፍ 16 ቊጥር 2-3 ላይ “እግዚአብሔር ቃል ወደዚህ ዓለም ይመጣ ዘንድ፣ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ሥጋን ይዋሐድ ዘንድ ምንአተጋው? በጨርቅ ይጠቀለል ዘንድ፣ በበረት ይጣል ዘንድ፣ ከሴት /ከድንግል/ ጡት ወተትን ይጠባ ዘንድ  በዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ምን አተጋው? ሕግ አፍራሽ ጲላጦስ ይዘብትበት ዘንድ፣ በመስቀል ይሰቀል ዘንድ፣ በመቃብር ይቀበር ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ይነሣ ዘንድ ምንአተጋው? በፍዳ ተይዘን የነበርን እኛን ያድነን ዘንድ፣ ለእኛ ብሎ አይደለምን! በማለት አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት ቅዱስ
እለእስክንድሮስ በአንክሮ ገልፆታል፡፡ (ፊሊጵ. 2፥5-9፣ 1ኛ ቆሮ. 1፥21-25)፡፡
 

 

ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ የመሆን ምስጢር ነው፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ሲባል፣ ረቂቅ መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፣ ግዙፍ ሥጋ ግዙፍነቱን ሳይለቅ፣ ማለትም ግዙፍ ሥጋ ረቂቅ መለኮትን ግዙፍ ሳያደርገው፣ ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ሳያረቀው በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ተዋሕዶ ማለት ነው፡፡

ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ማለት ደግሞ፣ መለከት የእርሱ ያልሆነውን የሥጋ ባህርይ ባህርዩ አድርጎ፣ ሥጋም የእርሱ ያልሆነውን የሥጋ ባህርይ ባህርዩ አድርጎ ተዋሕደ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ነገር ቅዱስ ቴዎድስዮስ “ከተዋሕዶ በኋላስ ሁለት ባህርይ አንልም፤ እንደ ንጹሓን አባቶቻችን ክርስቶስ (መለኮት እና ትስብእት) በአንድ አካል፣ ሁለተኛ የሌለው አንድ እንደ ሆነ እንናገራለን እንጂ” በማለት አስተምሮናል፣ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎድስዮስ 82 37)፡፡

ቅዱስ ቄርሎስም “የሥጋ ገንዘብ ለቃል፣ የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ” በማለት አንድ አካል አንድ ባህርይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ሰው የሆነ አምላክ ነው፡፡ ከሥጋዌ (ሰው ከመሆን) በኋላም፣ መለኮት ከሥጋ ለቅጽበተ ዓይን እንኳ የተለየበት ጊዜ የለም፡፡ 

 

ጌታችን በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል የአምልኮ ስግደት ሰግደው፣ መብዓ ማቅረባቸው ፍጹም አምላክነቱን ያሳያል፡፡ ፍጹም
አምላክ እንደ መሆኑ ስግደትን አምሐን ተቀበለ፡፡ ፍጹም ሰው እንደ መሆኑም ሕፃን ተባለ፡፡ (ማቴ. 2፥9-11)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” እንዳለ፣ በሥጋ ማርያም በተፀነሰ ጊዜም ከአምላክነቱ ሳይለይ በእኛ ማደሩን አስተምሮናል፤ (ዮሐ. 114)፡፡

ምስጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተዋሕዶ መወለዱን የሚያስረዳ፣ የሰይጣንን ተንኮል ያፈረሰበት የማይመረመር አምላካዊ ጥበብ ነው፡፡

አባታችን አባ ሕርያቆስ አምላክ ሰው መሆነን እንዴት እንደሆነ ሲያስተምረን “ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፣ ሳይወሰን ፀንስሽው፤ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማሕፀንሽ ተወሰነ” በማለት ነበር፤ (አባ ሕርያቆስ፤ ቅዳሴ ማርያም . 46)፡፡

ሰው ከመሆኑም የተነሣ ከአምላክነቱ ምንም ምን የጎደለበት የለም፡፡ ሰው ሲሆን በአምላክነት ወዳልነበረበት ዓለም የመጣ ሳይሆን፣ እንደ አምላክነቱ በእቅፉ ወደተያዘችው ዓለም፣ የተጎሳቆለውን የሰውን ባህርይ በቸርነቱ ያከብር ዘንድ፣ ከኀጢአት በቀር የሰውን ባህርይ ተዋሕዶ፣ ፍጹም ሰው ሆነ እንጂ፡፡ 

 

የአምላካችን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋዌውን ነገር በአግባቡ ያልተረዱ ብዙዎች፣ ለእኛ ብሎ በፈቃዱ ያደረገው ቤዛነት “የመሰናከያ ዓለት” ሆኖባቸው በክህደት ይኖራሉ፡፡

እኛ ለምናምን ግን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት፣ አባቶቻችንም እንዳስተማሩን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ” እናምናለን፣ እንመሰክራለንም፡፡ የወልድን ሥጋዌውን ማመን የመዳናችን መሠረት ነውና::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም

 

የተምሮ ማስተማር ሰንበት /ቤት

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top