ትረካ

ትካዜ ላንድ አፍታ

በአስናቀች እንዳልካቸው

     ሌሊት ሊነጋ ወፎች ይንጫጫሉ የእያአንዳንዱ ሰው የሰአት መቁጠሪያ የሆነትም ዶሮዎች ጮኸው ጮኸው ትንፋሻቸውን ውጠው ከሰፈሩበት ቆጥ ለመውረድ እያንሰራሩ ነው መልካሙም በዛ ጎሕ በቀደደበት ወቅት የዛች የደሳሳ ጎጆውን የጭራሮ በር ከፍቶ በመውጣት የፀሐይን አወጣጥና የጮራዎችን አፈነጣጠቅ በማየት ተፈጥሮን እያደነቀ እንዲሁም ደግሞ ያቺ ጮራዋ ደስ የሚለውን ፀሐይና ከፊት ለፊት ያለውን ተራራ፣ዛፍ ከዛም አልፎ ደግሞ ሰማዩንና ምድሩን እኒህን ሁሉ የፈጠረውን አምላክ እያመሰገነ ሽንቱን ለመሽናት የእርሻውን መሬት አቋርጦ ከእርሻው እልፍ ብሎ ወዳለው ጫካ ሲገባ እኒያ ከሁለት አመት በፊት ሚስታቸው የሞቱባቸው አባት አቶ ገ/እግዚአብሔር የሚወዷቸው  ሚስታቸው ወ/ሮ አትጠገብ ከመሞታቸው በፊት በዚህ ሰዓት ከመኝታቸው ተነስተው ፀሎት የሚያደርጉበት ጊዜ ነበር ደህና ከባለቤታቸው ሀዘን የተነሳ ያንን የባቄላ አበባ የመሰለውን አይናቸውን አጥተው እንኳንስ ዳዊት ይዞ ማንበብ ይቅርና ልጃቸው መልካሙ እንኳን  ከሌለ ተነስተው ከእንስራ ውሃ ጠልቀው መጠጣት ተስኖቸዋል ምንም እንኳን ታዲያ ዳዊት ይዞ መድገም ቢሳናቸውም በዛ አንደበት ርቱእ በሆነ ከንፈራቸው እግዚአብሔርን ለማመስገን ለሊቱን ከጃንው ላይ ደረብ ያደረጉትን ኩታ እንደለበሱ ያ የማያይ አይናቸውን ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ህሊናቸውን ሰብስበው ማለትም በአንቃእድ ህሊና በስቂለ ልቦና ሆነው ‹ ተመስገን አምላኬ የእንስሳት ፈጣሪ በረቂቅ ስልጣንህ ሁሉን አሳዳሪ› እያሉ ምስጋናቸውን በመደርደር ከተቀመጡበት የመደብ አልጋ በመውረድ ያቺ ጮራዋ ያማረውን ፀሀይ ለመሞቅ ወጥተው ከዛች ከጎጆአቸው ታዛ ስር ካለችው በሐ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ሳሉ በድንገት የሚስታቸው አሟሟት ትዝ ሲላቸው ያን የጎርፍ ውሃ የሆነውን እንባቸውን ሲያፈሱ በተለይም ደግሞ ሚስቲቱ ሊሞቱ ሳያጣጥሩ በሰለለ ድምፅ ገ/እግዚአብሔር የልጄን የመልካሙን ነገር አደራ ብለው የተናገሯቸው ቃል በህሊናቸው ውስጥ እያቃጨለ እረፍት ነሳቸው፡፡

ትንሽም ቁጭ እንዳሉ ልጃቸው መልካሙ ከየት መጣ ሳይሉት አጠገባቸው ቆሞ ኖሮ ዛሬ ደግሞ ምን ሆነሀል አባባ ብሎ ብሎ ሲጠይቃቸው ልጃቸውን ቅር እንዳይለው ብለው የፊጻቻን ገፅታ ለመለወጥ እየሞከሩ አይ ምንም አልሆንኩም ይህ አይኔ ደግሞ ስለተነሳብኝ እየቆረቆረና እየለበለበ ስላስቸገረኝ ነው ብለው መልስ በመስጠት ሊደብቁ ቢሞክሩም መልካሙ የአባቱን ፊት በማየት ምን ሲያስቡ እንደነበር ስለተረዳ አይ አባባ እውነቱን ንገረኝ እንጂ ለምን ትደብቀኛለህ የእማማ መሞት ያጎደለው አንተን ብጫ ሳይሆን እኔንም እንደሆነ ታውቃለህ ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ እንባው በነዛ በጎርፍ ታጥበው የተሸረሸረ መሬት በመሰሉት ጉንጮቹ ላይ በመንታ ይወርድ ነበር፡፡

አባቱም ተወኝ ልጄ ተወኝ እያሉ የሳቸውን ስሜት ደብቀው እሱን ለማፅናናት ቢሞክሩም መልካሙ እናቱ የሞቱት ነፍስ ካወቀ ነበርና የእናቱ ውበት ደም ግባት እንዲሁም የእጃቸውና የእግሮቻቸው ጣቶች በተለይም ያ ጥቁር ሀር የመሰለ ፀጉራቸው እየታወሰው የሰቀቀን እንባ ያነባ ነበር አባቱ ምንም እንኳ ሲሄድ ባይሰሙት ድምፁ ጥፍት ስላለባቸው መልካሙ አለህ ሄድህ ብለው መኖሩን ሳያረጋግጡ መልካሙ በለሰለሰ አንደበታቸው ልጃቸውን ለመምከር እንዲህ ሲሉ ጀመሩ አየህ መልካሙ መቼም ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ከሞት የሚቀር የለምና ምንም እኳን የእናትህ አሟሟት ዘወትር ቢያሳቅቀንም ብለው የጀመሩትን ሳይጨርሱት ፀጥ አሉ እስከ ትንሽ ጊዜም በመልካሙና በአባቱ መካከል ፀጥታ ሰፈነ በዚያን ጊዜ ነበር መልካሙ ወፎች ሰዎችን ለማፅናናት የተፈጠሩ መሰለው የታዩት ምክንያቱም እሱና አባቱ በሀሳብ ሰመመን ውስጥ ሳሉ የነቃቸው የወፎች ጩኸት ነበር ትንሽም እንደቆዩ ከእንቅልፍ እንደነቃ ሰው እህህ ብለው ይሁንና እንደው እኛ የሰው ልጆች መሽቶ ሲነጋ በእድሜአችን ላይ አንድ ቀን የቀጠልን ቢመስለንም በዛው መጠን ወደሞት አንድ ቀን እየቀረብን መሄዳችንን አትዘንጋ ደግሞኮ እግዚአብሔር እናትህን ከኛ ነጥሎ መውሰዱ ቢወዳት ቢመርጣት ነው እንጂ ጠልቶ አይደለም ፡፡ እንዲያውም እኛ ደጉ አባቴ ነድሳቸውን ይማርና ቄሰ ገበዝ ማንደፍሮት ሲናገሩ ስሰማ እግዚአብሔር የሚወዳቸውን ይቀጣቸዋል ወይም ደግሞ ይፈትናቸዋል ይሉ ነበር ዛሬ ግን እኔ ልጃቸው ከእሳቸው እውቀት ሲሶውን እንኳን ባለመያዜ እንደ ውስጥ እግር እሳት ያንገበግበኛል ቢሆንም ይቺይቺ እንኳን ዘወትር ስለሚናገሯት አትጠፋኝም እንዲያውም እግዚአብሔር የሚወዳቸውን እንደሚፈትን ሲናገሩ እንደው በአንድ አገር ላይ የሚኖሩ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ አንድ እዮብ የሚባል ታላቅ ባለፀጋ ሰው ነበር ይህም ሰው ከሀብቱ ብዛት የተነሳ ዘወትር ደስተኛ ነበር በኃላ ግን እግዚአብሔር እሱ ባወቀ ሲፈትነው ሃብቱን ንብረቱን አወደመበት ቀጥሎም ደግሞ ልጆቹን ገደለበት እንዲያውም ይባስ ብሎ እሱን እራሱን ሰውነቱን እያሳከከው በሽተኛ ያልጋ ቁራኛ አደረገው የሚገርመው ደግሞ ሰውነቱን ከማከኩ የተነሳ እጆቹ ዱሽ ሆነው በገል ስባሪ ያክ ነበር እሱ ግን ይህ ሁሉ ሲሆን የሰጠ ቢነሳ የለበት ወቀሳ እያለ እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር ታዲያ ሚስቱ ህመሙ ሲጠናበት አይታ መሞትህ ካልቀረ ብለው አይ ሴት ሴት እኳ ለሁሉ ችኩል ናት ሲሉ መልካሙ ምነው አባባ ለምን እንዲህ ትላለህ እንደውም ሴቶች አርቆ  አሳቢዎች ብልሃተኖች ናቸው ቢላቸው የለ አንተ አታውቅም እንዲያውም እኛ ደጉ አባቴ ሲናገሩ ሰው የሚኖረው የሚኖረው ከገነት የወጣው እንደውም ከነታሪኩ ልንገርህ ብለው እግዚአብሔር ሰዎችን ሲፈጥር በመጀመሪያ አዳምንና ሔዋንን ፈጠረ ሲሉ መልካሙ ታሪክ ለመጨረስ ልቡ ጎጉቶ ስለነበር አይ አባባ የበፊቱን ጨርስልኝ እንጂ ለምን ወደ ሌላ ትገባለህ ቢላቸው እህ ምን ብዬ ነበር ያቆምኩት ሲሉ መሞትህ ካልቀረ እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው እሱ ግን የሰጠ ቢነሳ ምን አለ ወቀሳ እሱ ሰጥቶኝ እሱ ቢወስድብኝ ለምን እሰድበዋለሁ ብሎ ገሰፃት ይሉ ነበር እና አሁንም እኔም ሆንኩ እናትህ እግዚአብሔ ፈቃድ ሲሆን አንተን ሰጠን ደግሞ እርሱ ራሱ ፈቅዶ እሷን ወሰደ ታዲያ እኛስ የሰጠ ቢነሳ ምን አለ ወቀሳ ብለን አንተወውም ብለው በጥያቄ አንገታቸውን ዘንበል አረጉ እሱም ቀበል በማድረግ አይ አባባ እስከ ዛሬ ባለማወቃችን እግዚአብሄርን አማረነዋል ከእንግዲህ ግን አናማርረውም ብሎ በል አሁንም ፀሀይዋ ስለጠነከረች ወደ ቤት እንግባ ብሎ በአንድ እጅ ወገባቸውን በአንድ እጅ ደግሞ ልብሳቸውን ሰብስቦ እየመራቸው ወደ ቤት ገቡ፡፡

Scroll to Top