ሐሙስ
አዲስ ኪዳን የተደረገበት ዕለት
ይህች ልዩ ዕለት ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከማይችሉ ከእንስሳት ደም፣ ኃጢአትን ሊያስወግድ ወደሚችል ወደ ክርስቶስ ደም የተሸጋገርንበት፣ ፍጹም ድኅነት ከማያሰጥ ከኦሪት መስዋዕት፣ የዘላለም ድኅነት ሊሰጥ ወደሚችል ወደ አዲስ መስዋዕት የተሸጋገርንባት ናት፡፡
“ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፡፡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡” (ማቴ 26፡26-28) ብሏልና፡፡
ስለሆነም ይህ የአዲስ ኪዳን ውል የተከናወነበት ዕለት፣ ለክርስቲያኖች ልዩ ዕለት ነው፡፡ ጌታ የሐዋርያት እግርን በማጠብ ዕድል ከእርሱ ጋር እንዲኖራቸው ካደረገ በኋላ (ዮሐ 13፡8) ወደ ሌላው ዕድል አሳትፎአቸዋል፣ ይህም የተለያዩ ጥቅሞችን የሚያድል አዲስ ኪዳን ቁርባን ነው፡፡ በዚህ በክቡር ሥጋውና በቅዱስ ደሙ የሚገኙ ጥቅሞች፡-
1. ከክርስቶስ ጋር ሕብረት ፈጥሮ መኖር
“ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ” (ዮሐ 6፡56)
2. ከእርሱ ጋር በመኖር መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት
“በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም…ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል” (ዮሐ 15፡1-5)
3. የኃጢአት ሥርየት ማግኘት
“ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡” (ማቴ 26፡26-28)
“የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” (1ኛ ዮሐ 1፡7)
4. የዘላለም ሕይወትን መጎናጸፍ
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” (ዮሐ 6፡53)
5. በማይራብና በማይጠማ ሕይወት መኖር
“የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም” (ዮሐ 6፡35)
6. በክብር ትንሣኤ መነሣት
“ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” (ዮሐ 6፡54) ብሏል፡፡ በመጨረሻው ዘመን ኃጢአት ያደረጉ የማይነሡ ሆነው አይደለም፡፡ የቆረቡ ሰዎች የሚነሡት ትንሣኤ የክብር ትንሣኤ ስለሆነ እንጂ “በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና” (ዳን 12፡2)
ለክብር ፈጥሮን፣ ባረጀ ሕይወት የኖርነውን ወደ አዲስ ሕይወት አሸጋግሮን፣ ነገር ግን ባለመታዘዛችን ምክንያት ወደ ዘላለም እፍረት ከመሄድ፤ ልባችንን ለንስሐ አሰናድቶ፣ ወደ ሥጋ ወደሙ ቀርበን፣ የሰጠንን የአዲስ ኪዳን መስዋዕት ተቀብለን፣ በቀኙ ለመቆም ሁላችንንም ያብቃን፡፡ አሜን!!!

