ስለ እኛ መሰቀሉን ይታወሳል
በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን በርካታ ሥርዓቶች የሚፈጸሙ ሲሆን ለአብነትም ያህል ሥዕለ ሥነ-ስቅለትና ልዩ ልዩ የቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት ከቤተ መቅደስ ወጥተው ከመቅደሱ በር ላይ ይደረደራሉ፣ ካህናትና ምዕመናንም ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስቱ ሰዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱ ይውላሉ፡፡ ይኸውም ጌታችን እርጥቡን ግንደ መስቀል ተሸክሞ ወደ መሬት ሦስት ጊዜ ወድቆ መነሣቱን ለማሰብ ነው ስለ መተላለፋችን መከራን የተቀበልክ አምላክ ይቅር በለን፣ ታረቀን ሰላምን ስጠን ስድባችንን አርቅልን፣ መርገማችንን ሻርልን በምሕረትህ እየን ለማለት መከራውን እናስባለን፡፡
በዘጠኝ ሰዓትም ካህናት በጥቁር ካባ ተሸፍነው ቁጭ ይሉና በሚያሳዝን ዜማ ደጋግመው “አቤቱ ይቅር በለን” ይላሉ፣ ሕዝቡም እንደ እነሱ ያዜማሉ፣ ይኸውም ነፍሳት በጨለማ ሲኦል ሆነው ለ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን ያሰሙትን ጩኸት ለማዘከር ነው፡፡
በሰሞነ ሕማማት ውስጥ በማሰብ፣ በማየት፣ በመናገር፣ በገቢር የተፈጸመ ኃጢአት ቢኖር ምእመናን ካህኑ ፊት ቀርበው ይናዘዛሉ. ይህም ኃጢአትን ሁሉ የሚያስተሰርይ ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሆኖ የምሕረት አዋጁን ለሰው ልጅ ሁሉ ማሰማቱን ለመግለጥ ነው፡፡
እንደዚሁም ከኑዛዜው ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ሥርዓት አለ እርሱም ጥብጣቤ ይባላል፡፡ ስንብት ከመደረጉ በፊት ካህናት የወይራ ዝንጣፊ ይዘው በፊታቸው ቀርቦ የሚናዘዘውን ምዕመን ጀርባ እየጠበጠቡ ይህን ያህል ስገድ እያሉ ያውጃሉ፡፡ ሁሉም የታዘዘውን ይሰግዳል የስግደቱ ትርጉም እንደላይኛው ሲሆን የጥብጣቤው ትርጉም አይሁድ ከሕጋቸው ውጪ እየተፈራረቁ 6666 ጊዜ እንደገረፉት ለማሰብ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ጌታችን በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ስለሆነ ሥርዓተ ቅዳሴ አይፈጸምም፡፡ በ 11 ሰዓት ሊቃውንት መቋሚያ ላይ ጧፍ አብርተው ዙሪያውን በመክበብ ከመዝሙረ ዳዊት የተለያየ ክፍል እያስተዛዘሉ ይሉና በመጨረሻም ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለ ውሉደ ወልዱ ይደምሰስ›› “ይሁዳ ልጁም የልጅ ልጁም ይደምሰስ” ብለው በርቶ የነበረውን ጧፍ ቀጥቅጠው ያጠፉታል፡፡ ጧፉን መምታታቸው፣ ይሁዳ ክብሩን በማቃለሉ መውደቁን፣ ቀጥቅጠው ማጥፋታቸው ሰውን ያሳተው ዲያብሎስ በመስቀል ኃይል መመታቱን፣ ድል መነሣቱን ለማዘከር ነው፡፡
በመቀጠልም ሊቃውንት ‹‹ንሴብሆ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› የተመሰገነ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን በማለት ይዘምራሉ፣ ይኸም በሞትህ ሞትን ሻርህ ጠላትን ደምስሰህ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ከሲኦል ወደ ገነት አገባኸን ሲሉ ነው፡፡
ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ሁላችንንም ያብቃን፤ አሜን!!!

