የረዕ ጾም መነሻ ምሥጢር ይህ ነው!የረቡዕ ጾም መነሻ ምሥጢር ይህ ነው!
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞት ተወሰነበት፡፡ ይህ ዕለት በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ሲታሰብ ይኖራል!
አንድነት ሳይኖራቸው፣ የእምነትም የአመለካከትም ስምምነነት የሌላቸው፤ ግፍ ለመሥራት ሲሆን አንድነት የፈጠሩ፣ ከክፉ ማኅበራት መካከል፡- “በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ” (ማቴ 26፡3-4) ችግር የሆነባቸው ግን “እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበር” (ሉቃ 22፡2) ወቅቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር የጠፋበት፣ ሰው ብቻ የሚፈራበት እንደነበር በዚህ ይታወቃል፡፡
ከተሰብሳቢው መካክል መንፈስ ቅዱስ አፉን ከፍቶ፣ ፊቱን ጸፍቶ ስለ ዓለም ሁሉ መዳን መልካም እንዲናገር ያደረገው “በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው፡፡ ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ” (ዮሐ 11፡48-51)፡፡
በስብሰባው ዕለት፣ ምልዓተ ጉባኤው የወሰነው፣ ከሕዝብ ጋር ጠብና ሁካታ ከመፍጠር፣ ማስታወቂያ በቤተ መቅደስ፣ በፍርድ ሸንጎ፣ እንዲሁም ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ መናገር ሲሆን፤ ይህም “ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቀው ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው” አዋጁ መነገሩን መጽሐፍ ይነግረናል (ዮሐ 11፡57)፡፡ ረቡዕ ዕለት ከአሥራ ሁለቱ አንዱ “የአስቆሮቱ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፡፡ ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ?” (ማቴ 26፡14-16) አላቸው፡፡ እነርሱም ጌታ ያለበትን ሁነኛ ስፍራ የሚያውቅ ሰው ስላገኙ በደስታ፣ ከእርሱ ጋር ስምምነት አደረጉ፡፡
ከይሁዳ ጋር ተባባሪ የሆነው ማን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲጠቁመን “ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ” ይላል፡፡ ቀድሞም በገንዘብ ፍቅር እንዲታወር ያደረገው አጋሩ ዲያብሎስ ነውና፣ “ያዳቆነ ሰይጣን…” እንዲሉ፡፡ “ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ፤ እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ፤ እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር” (ሉቃ 22፡3-4)፡፡
ይህች ዕለተ ረቡዕ፣ እንዲገደል የተወሰነበት በመሆንዋ ክርስቲያኖች ሁላችን ዕድሜ ልካችንን ለእኔ ስትል ሞት እንድትሞት ተወሰነብህ በማለት በጾም እናስባታለን፡፡ ስለ እኛ ክፉ ተመከረበት፣ ክፉ ተወሰነበት፣ ዝም እንደሚል በግ በሸላቶቹ ፊት ዝም ብሎ ፍርዱን ተቀበለ እያልን እናስበዋለን፡፡
በሞቱ ፍርድ፣ እኛን ከገሃነም ፍርድ ያድነን፡፡ አሜን!

