ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቃዋሚዎች ለሚጠይቁት ጥያቄ
እንደአጠያየቃቸው የመመለስን ጥበብ ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡
አምላካችን ለሚቀርብለት ጥያቄ የሚመልሰው መልስ ያስገርማል፤ እነርሱ በተንኮል ሊያጠምዱት ነው የሚፈልጉት፤ እርሱ በአምላክነቱ የልባቸውን ያውቃል “ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበር” እንዲል (ዮሐ 2፡25) ለመማር ስላልመጡ እያንዳንዳቸው በተንኮል ለሚጠይቁት ጥያቄ እርሱ የተንኮል መልስ የለውምና፤ ተገቢ መልስ ይሰጣቸው ነበር፡፡ በዚህ እኛን በተንኮል ለሚጠይቁ ለዘመናችን መናፍቃን አብነት ሆኖናልና እንዴት እንደምንመልስ፣ ሌሎቹን ጥያቄና መልስ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የሚሰጠውን ትምህርት እንድትማሩ እየጋበዝኩ፤ በዚህ ፌስ ቡክ አንዱን ፈጣሪያችን ለእኛ ያስተማረበትን ጥበብ ለጊዜው እንቅሰም እጋብዛለሁ፡-
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች፡- “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ”
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች፡- ለመጠየቅ ዝግጁ ነበሩ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ “የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?”
በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ለመዋሸትና እውነትን ለመደበቅ ስለፈለጉ ዞር ብለው እርስ በርሳቸው “ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ” ልብና ኩላሊት በሚመረምረው አምላክ ፊት ቀርበው በመዋሸት መልሳቸውን ተናገሩ፡፡
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች፡- “አናውቅም” አሉት።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም” አላቸው፤ “እኔም አላውቅም” ብሎ አልዋሸም፤ በአንደበቱ ሐሰት የለበትምና፡፡ (ማቴ 21፡23-27)
ስለዚህ ምእመናን ከጌታ በተማርነው መሠረት ከማይቀበሉን መናፍቃን ጋር በክርክር መዋል አይገባንም፡፡ የሚያምኑ ከሆነ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜ መልስ ሰጥተን፣ መለየት ተገቢ ነው፤ ስለ ጌታ አምላክነት፣ ስለ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ ስለ መላእክት ተራዳኢነት፣ ስለ ጻድቃን ጸሎትና ስለ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውንና የምናምንበትን አንድ መልስ ነግረን፤ በዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ታምናላችሁ? ስንል ካላመኑበት በመሟገት መዋል ተገቢ አይደለም፡፡ ለማያምን ሰው “እኔም አልነግራችሁም” በማለት ከእንዲህ ዓይነት ሰው መራቅ ተገቢ ነው፡፡
“መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ” (ቲቶ 3፡10) ተብለናልና፡፡
