የሕማማት መታሰቢያ ዕለተ ሰኞ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ በሆሣዕና እሁድ ዕለት “አሁን አድን” የሚለውን ዝማሬ ከቀረበለትና ከሁሉም ልመናን ከሰማ በኋላ በቤተ መቅደስ ሕሙማነ ሥጋን ፈውሶ፣ ከቤተ መቅደስ ከወጣ በኋላ በቢታንያ አድሮ የነፍስን ፈውስ የሚሰጥበት ቀን ቀርቧልና በኢየሩሳሌም ተገኝቷል (ማቴ 21፡17)፡፡ በዕለተ ሰኑይ ተራበ (ማር 11፡11) ዐይኑን በለስ ላይ ዐሳረፈ፤ ወደ በለስም ሄዶ ፍሬ ፈለገ፣ ነገር ግን ፍሬ አላገኘባትም፡፡
ምንም ቅጠልዋ ሰፋፊ፣ ፍሬዋ ጣፋጭ ቢሆንም፤ በጊዜው ግን ፍሬ አላገኘባትምና፣ ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ ምሥጢር ያለው ንግግር ነበር፡፡ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ዛሬ 11፡30 ላይ ለስግደት በቤተ ክርስቲያን ቢገኙ፤ በሁሉም የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሰፊው ተብራርቶ ይማሩበታል፤ ይመከሩበታል፡፡
ለጊዜው ለራሳችን መልእክት ለማሳሰብ ያህል፤ ይህች በለስ ልክ በወይኑ መካከል እንደተተከለችው በለስና በየዓመቱ ፍሬ እንዳልተገኘባት እንዲሁም ትቆረጥ ተብሎ እንደተፈረደባት የበለስ ዛፍ፤ እኛም ክርስቲያኖች በእምነት ብቻ ሆነን፤ ፍሬ ካልተገኘብን ሞተን፣ ለፍርድ ቀን፣ በግራ ቆመን፣ “እናንተ ርጉማን” በመባል እንደሚፈረድብን ያሳያል፡፡ እስከ አሁንም የቆየነው በቅዱሳኑ ምልጃ ነው፡፡ ያለ መልካም ፍሬ ተገኝተን እንዳይፈረድብን በቸርነቱ፣ በእመቤታችን ምልጃ፣ በመላእክት ጥበቃ፣ በጻድቃን ጸሎት፣ ሁላችንንም በፍሬ እንድንገኝ ይርዳን! (ሉቃ 13፡6-9)፡፡ አሜን!!!

