ታቦተ መድኃኔዓለም

የመድኃኔዓለም ፅላት በ፲፰፻፺፭ ዓ.ም በግርማዊ ዳግማዊ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ትዕዛዝ በመምህር ፈቀደ እግዚእ ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰዶ ሲፀለይበት ቆይቷል፡፡

“ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ን.ነ.ዘ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ፲፱፻፵፫ ዓ.ም እንደጻፉት ንጉስ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደት እንዳሉ ልመናቸውንና ፀሎታቸውን የሚያቀርቡበት በእምነታቸው ላይ ምግባራቸውን የሚያጠናክሩበት ቤተ ጸሎት ስለቸገራቸው አንድ ጽላት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ስላሰቡበት ወደ እየሩሳሌም ለእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ በጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም እንዲህ የሚል መልዕከት ላኩላቸው  “የእግዚአብሔርም ቸርነት ፈቅዶልንና አሰናብቶን ወደ እየሩሳሌም እስከምንመጣበት ቀን ድረስ የሃይማኖት ችግር እንዳያገኘን የሚያድጉትም ልጆች የሃይማኖታቸውን መሠረት እንዳያጡት አስበን አንድ ጽላትና አምስት መነኩሳት የሚያስፈልገውን ንዋየ ቅዱሳትና መጽሐፍ ሰጥተውት ይዞ እንዲመጣ አባ ሐናን ልኬዋለሁና ከመምህር ገሪማ ጋር ተማክራችሁ ዓቢይ ጾም ሳይገባ እንዲደርስ አድርጋችሁ እንድትልኩልን ይሁን ብለውበላኩላቸው መሠረት እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ድረስ በስደት ያለች የኢትጵያ ቤተክርስትያንእየተባለበሃገረ እንግሊዝ በስደት የሚገኙ ንጉሣውያን ቤተሰቦችና ለሌሎች ምዕመናን ለሥርዓተ አምልኮ መፈፀሚያ እንዲሆን በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ ከአምስት ልኡካን ጋር በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ሎንደን ሄዶ እስከ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም እንግሊዝ ሀገር አገልግሎአል፡፡የመድኃኔዓለም ታቦት በነሐሴ ፲፫ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ግርማዊት እቴጌ መነን አዲስ አበባ በገቡበት ቀን አባ ኃይሌ ቡሩክ የተባሉት መነኩሴ ይዘውት ገብተዋል፡፡ ታቦቱም በቤተ መንግስት የተለየ ቦታ ተደርጎለት በአባ ኃይሌ ቡሩክ ጠባቂነትና አጣኝነት ከቆየ በኋሏ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፭ ዓ.ም ተመልሶ ቀድሞ ቀ.ኃ.ሥ በዛሬው የካቲት ፲፪ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ምሥካየ  ኅዙናን በመባል ተሰይሞ ተተክሎ ነበር፡፡

የምሥካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም መነኮሳት በኅብረት ለመኖር /የአንድነት ኑሮ/ ለመኖር በመስማማታቸው በግንቦት ፲፮ ቀን ፲፱፻፴፯ ዓ.ም በብፁዕ እጬጌ ገብረጊዮርጊስ /በኃሏ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባሰልዮስና/ ሌሎች መምህራን ሊቃውንት በተገኙበት በዚሁ ስፍራ በቅዳሴ ተከብሯል፡፡

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አዲስ ህንፃ ቤተክርስቲያንለመስራት በሚያዚያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵ ዓ.ም በ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ የመሠረት ድንጋዩ ተጣለ የተጣለውም በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ክበብ ውስጥ ነው:: በዚህ ሥፍራም እንዲሠራ የሆነበት ምክንያት ለተፈሪ መኮንንና ለእቴጌ መነን ተማሪዎች ሲባል እንደሆነ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል ፡፡ መሰረት የተጣለበት ወቅትም የተማሪዎች የሃይማኖት ተቃውሞ በተደረገበት ዓመት መሆኑ ይህንኑ ያመለክታል ፡፡ የቤተክርስቲያኑ ሥራ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም ሚያዚያ ፳፯ ቀን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀ.ኃ.ሥ. ግርማዊት እቴጌ መነንና ሌሎቹም በተገኙበት ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡ የመጀመሪያውም አስተዳዳሪ አባ ሐና ጀማ ሆነው አገልግለዋል፡፡

አበበ ከበደ ና ጓደኞቻቸው ከተፈሪ መኮንን ት/ቤት ወጥተው በከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው መደበኛ ሥራ ላይ እንደ ተሰማሩ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የጠነሰሱትን የዚያን ጊዜውን ጥምረታቸውን እንደገና አጎልብተው የሚያስቡትን ለመፈጸም እንዲችሉ አመቺ ጊዜን በመጠበቅ በየጊዜው እየተሰባሰቡ ይወያዩ ነበር፡፡አባ ተክለማርያም በጻፉት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አመሰራረት በሚለው መጽሓፋቸው አምስት ወይንም ስድሰት በመሆን ከ፲፱፻፴፯ ዓ፣ም ጀምሮ  በቤተክርስትያን ጥላ ስር ለመሆንና ማኅበር ለመመስረት ይጠይቁ ነበር ብለዋል፡፡

በም/ኅ/መ/ገዳም ጥላ ሥር ለመሰባሰብ ሲሞክሩ በዚያን ግዜ ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ የገዳሙ የበላይ ጠባቂ ከነበሩት አባ ሀና ጅማ ከአስተዳዳሪው መምህር ተክለ ማርያም ያገኙትን ይሁንታና ድጋፍ መሠረት በማድረግ አቶ ገብረ ጊዮርጊስ አጋዤ የመሳሰሉትን እንዲሁም ተሥፋዬ ሙሉሸዋ ና ግርማቸው ብዙነህ ዘበንጉሥ ውሂብ መርጊያ ጎበናንና ሌሎች በስም ያልተጠቀሱትን ቀላቅለው ያዋቀሩት መድረክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን ተምሮ ማስተማር ማኅበርን አስገኝቶ  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስትያን ጥላ ሥር ከተዋቀሩት ማኅበራትና ሰንበት ት/ቤቶች በዘላቂነት ረዥም ዕድሜ ለማስቆጠርየበቃ መንፈሳዊ ማኅበር ለመመሥረት በቅተዋል፡፡( የተምሮ ማስተማር ማኅበር አመሠራረት አጭር መግለጫ)

በተጨማሪም ሊቀሥልጣናት ሀብተማሪያም ወርቅነህንና (በኋላ አቡነ መልከጼዲቅ) በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በግብረገብ መምህርነት ተመድበው ሲያስተምሩ የነበሩትን አባ መዐዛ ቅዱሳንን (በኋላ አቡነ ናትናኤል) ጋር በመሆን በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም ከተፈሪ መኮንን እና ከእትጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር  የተምሮ ማስተማር ማኅበርየሚል ስያሜና መተዳደረያ ደንብ እንዲጸድቅለት አድርገዋል፡፡

ተምሮ ማሰተማር የሚለውን ስያሜ ያወጡት ገብረ ጊዮርጊሰ አጋዤ  እንደሆኑ ከቀሲስ ታደሰ መንግሥቱ ከመርጌታ ረታ አሳልፍና ከመምህር ታዬ አብርሃም እንዲሁም ከልጃቸው ሲ/ር የሺመቤት ገብረ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል፡፡

Scroll to Top