መንፈሣዊ ተዐምርና የፕሬቮ ምስጢራዊ ሪፖርት

ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረወልድ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሲማሩ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ከእርሳቸው ጋር የኖረናሳይናገሩ ማለፍ የማይችሉት  አንድ የተፈጠረ አስደናቂ መንፈሳዊ ተአምር አለ ሲሉ ለዚህ ጥናት አቅራቢ እንባ እየተናነቃቸው ሲገልጹ“ እግዚአብሔር እኔን ይጎትተኛል እኔ ግን እሸፍታለሁ”በማለት  እነዚያ ብለው በመጀመር ስለ ኢየሱሳውያን ጄስዊቶች ቀጥለዋል፡፡

እነዚያ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የውጭ አገር ተወላጅ አስተማሪዎቻችን የሚኖሩት እዚያው ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ በጋራ እራት በልተው ወደ ጋራ ጸሎት ቤታቸው ሄደው ጸሎት ካደረሱ በኋላ ሲጨርሱ ወደ የመኖሪያ ቤታቸው የመሄድ ልማድ ነበራቸው፡፡

አንድ ቀን ግን  ማታ ቀደም ብዬ አማካሪዬ ሆኖ ወደ ተመደበልኝ መምህሬ ወደ ነበረው ሚስተር ፕሬቮ መኖሪያ ቤት ስሄድ አማካሪዬ ከጋራ ጸሎት ቤት ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ እቤታቸው ደረስኩ፡፡ ተማሪዎች ወደ የአማካሪዎቻችን ቤት ስንሄድ በቤት ውሰጥ ከሌሉ እስኪሚመጡ ድረስ ሻይ አፍልተን በዚያን ጊዜ ለእኛ ተማሪዎች ብርቅ የነበረውን ደረቅ ብስኩት በሻይ እየተመገብን አማካሪያችንን መጠበቅ የተፈቀደልን ቢሆንም ያ ዕለት እንደገባሁ ሚስተር ፕሬቮ ስላልነበሩ ሐሳቤ ወደ ሻይ ማፍላቱና ደረቅ ብስኩት መመገቡ ሳይሆን ምን እንደገፋፋኝ ሳላውቀው ወደ አማካሪዬ ጠረጴዛ ዓይኔን ወርወር ሳደርግ በመጻፍ ላይ የነበረ ሪፖርት  ተዘርግቶ አየሁ፡፡ ውስጤ ወደዚያው ደብዳቤ ስለመራኝ ወደ ጠረጴዛው ሄድኩና ያን ተጽፎ ያልተደመደመውን ሪፖርት ቁጭ ብዬ ማንበብ ጀመርኩ ሲሉ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገልጸዋል፡፡

ደብዳቤው የተጻፈው በፈረንሳይኛ ቋንቋነበር፡፡ ከፍተኛ ክፍል ለነበሩት ተማሪዎች ከእንግሊዘኛው እኩል ፈረንሳይኛም ይማሩ ስለነበረ በፈረንሳይኛ የተጻፈውን መገንዘብና ምንነቱን ማወቅ አልተሳናቸውም፡፡ ጽሑፉን ማንበብ በመጀመራቸው ከአንዱ መስመር ወደሌላው በሄዱ ቁጥር መላ ሰውነታቸውን እየወረራቸውና ፍርሀት ፍርሀት እያላቸው ተጽፎ ያልተቋጨውን ሪፖርት በቁጭትና በመባባት ስሜት ሆነው አንብበው ጨረሱት፡፡

ሰውነታቸው  በፍርሀት እየራደ ሳይለቃቸው አማካሪያቸው ሳይመጣ በፍጥነት ከቤታቸው ወጥተው ወደ መኝታ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ጥቅልል ብለው ለመኝታ ቤት ጓደኞቻቸውም ሳይነግሯቸው ተኝተው ማልቀስ ጀመሩ፡፡ ወደ አማካሪያቸው  ቤት ሲሄዱ ባንድ መኝታ ክፍል አምስት ያህል ሆነውና አብረው ከሚኖሩት አራቱ የመኝታ ቤት ጓደኞቻቸው እነ ታደሰ መንግሥቱ ወርቁ ተፈራ ሽፈራው መታፈሪያ ና ዶ/ር አክሊሉ ኃብቴ ዘወትር ከእራት በኋላ በተማሪዎች ዲን በሚስተር ዚፈል ተቆጣጣሪነት ይካሄድ በነበረው ከመመገቢያ ቤታችውና ጥናት ቦታ ሄደው የነበሩት ጓደኞቻቸው የጥናቱ ሰዓት ማለቂያ ደርሶ አንድ ባንድ አየተመለሱ ይመጡ ጀመር፡፡ ከአማካሪያቸው ሚሰተር ፕሬቮ ቤት ለምን ቀደም ብለው እንደተመለሱና ለምንስ ተጠቅልለው እንደተኙ በመጠየቅ ተነስተው ምክንያቱን እንዲነግሯቸው ቢጠይቋቸው  ሳይነግሯቸው ጥቅልል ብለውእንደተኙ ሲያለቅሱ አደሩ፡፡

በአማካሪያቸው በሚስተር ፕሬቮ መኖሪያ ቤት ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ያጋጠማቸውና ያነበቡት ያ በመጻፍ ላይ የነበረ ያልተደመደመ ሪፖርትና ደብዳቤ የተጻፈው ካናዳ ለሚገኘው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መምህራን ለመጡበት የኢየሱሳውያን (የጄዝዊትስ) ማዕከል ነበር፡፡ በመጻፍ ላይ የነበረው ደብዳቤ የሚናገረው ግራኝ መሓመድ ኢትዮጵያን በወረራት ዘመን ለዕርዳታ ከመጡት የፓርቹጋል ወታደሮች ጋር፣ ከዚያም በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስለገቡትና አጴ ሱስንዮስና መኳንንቶቻቸውን ወደ ካቶሊክ እምነት ስለ ለወጧቸው እነ ጴጥሮስ ፖኤዝ ሜንዴዝና ሌሎች የኢየሱሳውያን መነኮሳት ነበር፡፡ እነዚያ የኢየሱሳውያን መነኮሳት ንጉሠ ነገሥቱንና መኳንንቶቻቸውን ወደ ካቶሊክ እምነት ለውጠው የቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ካቶሊክ እምነት ለመለወጥ ጥረት ሲያደርጉ በተለወጡትና ባልተለወጡት ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙ ደም ያፈሰሰ ጦርነት እንዲካሄድና ብዙ ደም እንዲፈስ ምክንያት የሆኑትን የጄዝዊት መነኮሳት ስለፈጸሙት ስሕተትና መነኮሳቱ ምክንያት ሆነው በተሰሩት የጎንደር ቤተ መንግሥት ታላላቅ ሕንጻዎች፣ ድልድዮችና ሌሎች ስራዎች አጓጉተው ወደ ካቶሊክ እምነት የለወጧቸውን አጼ ሱስንዮስም ደጋግሞ የሚያነሳ ነበር፡፡

ደጃዝማች በዚያን ጊዜ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ እነፓኤዝናሱስንዮስ እነማን ናቸው? መምህራኖቹ እንደነ ጴጥሮስ ፖኤዝ ና አልፎንስ ማንዴዝ ቸኩለው እንዳይሳሳቱ በጥንቃቄ የሚሰሩት ስራ ምንድን ነው? የሚሉትንና በደብዳቤው የተጠቀሱትን ሌሎቹንም ጉዳዮች ሲያወጡና ሲያወርዱ ሲበሳጩና ሲያለቅሱ አድረው ጠዋት ወደ ትምህርት ክፍል መግባቱን በመተው ለአዳሪ ተማሪ ያለፈቃድ ወደ ትምሀርት ቤቱ መግባትና መውጣት የማይቻለውን ዋናውን በር ትተው ፣ ከትምህርት ቤቱ በስተሰሜን በኩል ባለው የሽቦ አጥር በመሹለክ ጥቅጥቅ ባለው የባህርዛፉ ጫካ ውስጥ አቆራርጠው ከእንጦጦ ከአሜሪካን ኤምባሲ በኩል ቁልቁል በሚመጣው ጎዳና በመግባት ፒያሳ በኪንግ ጆርጅ ቡና ቤት ተርታ በምዕራብ በኩል ወደሚገኘው ጃኖፖሎስ መጽሐፍት መሸጫ ሱቅ ገሰገሱ፡፡

መጽሐፍት መሸጫው ሱቅ እንደደረሱም፤ የሚገርም ተአምር ገጠማቸው፡፡ ይኸውም ገና ወደ መጽሐፍት መሸጫው ሱቅ ሳይገቡ ከመስታወት መስኮቱ ላይ የተደረደሩትን መጻሕፍት ሲመለከቱ በመጽሐፉ ጠንካራ ልባስ ላይ የተሸፈነ ሌላ ጥቁር የወረቀት ሽፋን ላይ በላዩ ሰንደቅ ዓላማ ያነገተ ቀይ ሞአ አንበሳ የሚገኝበት ርዕሱ “የአቢሲኒያ ታሪክ የሚል መጽሐፍ ተመለከቱ፡፡ ወደ ውስጥ ገብተው ሻጩን መጽሐፉን እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ኢንዴክሱን እያገላበጡሲያነቡ የሚስተር ፕሬቮ ደብዳቤ ውስጥ የተጠቀሱትን ስሞች ሁሉንም በማግኘታቸው መጽሐፉን ገዝተው ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ ማንም ሳያየቸው በወጡበት የሽቦ አጥር ሾልከው ይገባሉ፡፡

ወደ ትምሀርት ቤቱ ተመልሰው በገቡበት ሰዓት ተማሪው ሁሉ በየትምህርት ክፍሉ ገብቶ የሚማርበትና ግቢው እረጭ ያለበት ጊዜ ስለነበረ መኝታ ክፍላቸው አንሶላ ውስጥ ገብተውየገዙትን መጽሐፍ ኢንዴክሱን እየተመለከቱየሚፈልጉትን ርዕስ በመምረጥ ማንበብ ጀመሩ፡፡ መጽሐፉን ወደ ውስጥ ገብተው ሲያነቡ በግራኝ ወረራ ዘመን ለእርዳታ ከመጡት የፓርቹጋል ወታደሮች ጋር መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገቡትና በኋላም የመጡት አፄ ሱሱንዩስንና መኳንንቶቻቸውን ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲለወጡ ባደረጉት ምክንያት በኢትዮጵያውያን መካከል የተከሰተውን ሃይማኖታዊ ጦርነት፣ የሕዝብ እልቂትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውድመት በተገነዘቡት ቁጥር ሆዳቸው እየባባ ትላንት ማታና ሌሊት ሲያለቅሱ ያደሩት እየተባባሰ ስለሄደና በጣም አዝነው ስለነበረ፣በተጨማሪም ጠዋት ክፍል ስላልገቡና ምሳም ላይ በመመገቢያ ክፍል ስላልተገኙ፤ በመኝታ ቤትም ሆነ በትምህርት ክፍል አብረው ከሚማሩት ውስጥ የቅርብ ጓደኛቸው የነበረው ሽፈራው መታፈሪያ መኝታ ቤት እንዳሉ ለማየት ይመጣሉ፡፡ በጣም አዝነውእያለቀሱ ሲያገኛቸው ደንግጦ ምክንያቱን ይጠይቃል፡፡ ደጃዝማችም ትናንት ማታ አማካሪያቸው ሚስተር ፕሬቮ ቤት ሄደው ካነበቡት ደብዳቤ ጀምሮ ያለውን፣ ና ከገዙት መጽሐፍም ያነበቡትንና የተሰማቸውን የመረበሽ ሁኔታ ሲነግሯቸው እሳቸውም ማልቀስ በመጀመራቸው አብረው ብሶታቸውን ይወጡ ጀመር፡፡ ከዚያም ጉዳዮን በምስጢር ይዘው ለቅርብ ጓደኞቻችው ለመንገር ተስማሙ፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩን  አንድ በአንድ የነገሯቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው ወርቁ ተፈራ (በኋላ ቀ.ኃ.ሥዩኒቨርስቲ የሕግ አስተማሪና የሕግ ፋክልቲ ዲን የነበሩት)፤ ታደሰ መንግሥቱ ሽፈራው መታፈሪያና ለሌሎችም ለእያንዳንዳቸው የተነገራቸው ሁሉ ተሰባስበውና ጉዳዩን በምስጢር ይዘው ቁጥራቸውን ዐሥራ ሁለት በማድረግ ዘዴ ለመፈለግና ስራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን  ህቡዕ ማኅበር አቋቋሙ፡፡እነዚህም:-

  • ፩ አበበከበደ
  • ፪ አባተመንክር
  • ፫ አክሊሉ ኃብቴ ( ዶ/ር)
  • ፬ አሰፋ ተክለሥላሴ
  • ፭ ወልደሰማዕትገብረወልድ (ደጃዝማች)
  • ፮ ወርቁተፈራ
  • ፯ መኮንን ዋሴ
  • ፰ ስዩምወልደአብ
  • ፱ ተሰማአባደራሽ ( ኮሎኔል)
  • ፲ ታደሰመንግሥቱ (ቀሲስ)
  • ፲፩ ታደሰመታፈሪያ ና
  • ፲፪ ሽፈራውመታፈሪያ ነበሩ፡፡

*ተራ ቁጥር ፲፩ን ደጃዝማች ወልደሰማዕት ሊያሰታውሷቸው አልቻሉም ፐሮፌሰርመሥፍን ወልደማሪያም ይሆኑ እንደሆነ ተጠይቀው እርሳቸው በኋላ ላይ ተጨምረው ይሆናል እንጂ ከ፲፪ቱ ውስጥ የሉበትም ብለው ለዚህ ጥናት አቅራቢ ነግረውታል፡፡ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያምን ለመጠየቅ የተደረገውጥረትአልተሳካም፡፡

*የስም አፃፃፋቸው አ በ ገ ደ……. የሚለውን የፊደል ቅደም ተከተል መሰረት በማድረግ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አባላት በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም ህቡዕ ማኅበር እንዳቋቋሙ ታደሰ መንግሥቱ በቃለ ምልልስ ላይ በምስልና በድምጽ ሁሉንም በስም ባይጠቅሱአቸውም የተወሰኑትን በመግለጽ ያረጋገጡት ሲሆን አበበ ከበደም በተለያየ ጽሑፎች ላይ በ፲፱፻፴፱ መሰባሰብ እንጀመሩ ይገልጹታል፡፡ ደጃዝማች ግን ሁኔታውን ከጳጳሳት ሹመት ጋር በማያያዝ በ፲፱፻፵ ይመስለኛል ይላሉ፡፡ ይሁንና አበበ ከበደ በእንግለዝኛ ለእርዳታ ማሰባሰቢያ ዐላማ በጻፉትና ና በፈረሙበት ደብዳቤ እ.ኤ.አ  በ፲፱፻፵፯ እንደ ተጀመረ ስለገለጸ ይህ ደግሞ ፲፱፻፴፱ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡የተምሮ ማሰተማር ማኅበር ዓመታዊ መጽሄቶች ላይ በተደጋጋሚ ፲፱፻፴፱ በሚል ተገልጾአል፡፡ ምን አልባት ኅቡዕ ማኅበሩ ተሰብስቦ ስራውን ጀምሮ በወቅቱ ጉዳዩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስኪደርስ ወራትን ፈጅቶ ወደ ፲፱፻፵ ተሻግሮ ይሆናል፡፡ በበርካታ ጽሁፎች ላይና ቃለመጠይቅ ላይ እንደተገለጸው ግን  በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም ነው፡፡(የተምሮ ማስተማር ማኅበር ፲ኛ ና ፲፭ኛ ዓመታዊ በዓል አከባበር መጽሔት)

ኅቡዕ ማኅበሩ እየተሰባሰበ መመካከር እንዲችል፣አንድ ዘዴ መፈጠር ነበረበት ምክንያቱም የሚሰበሰቡበት ዐላማ ከታወቀ ከትምህርት ቤቱ መባረርን ከማስከተሉም በላይ ንጉሠ ነገሥቱ ከሠሙም በልመናና በእርዳታ በብዙ ድካም የመጡትን መምህራን ማስቀየም ጉዳቱ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነበር፡፡

ስለዚህም የተገኘው መላበትምህርት ቤቱ የሚገኙትን መጥፎ ጠባይ ያላቸውን  የመኳንንት ልጆችና ሌሎች በትምህርትየሚያስቸግሩትን ተማሪዎች ለመምከርና የተጣሉትን ለማሰታረቅ እንድንችል መሰብሰብ እንዲፈቀድልን በማለት ዲን የነበሩትን ሚስተር ዚፈልን መጠየቅ ነበር፡፡ እሳቸውም አንዳንድ ተማሪዎች የአልኮል መጠጥ እየጠጡ ረብሻ ና ድብድብ ይፈጥሩ ስለነበር ሃሳቡን በደስታ ተቀብለው “ብትፈልጉ ከትምህርት ክፍሎች አንዱን መርጣችሁ ወይም በምትመርጡት መኝታ ቤታችሁ ሆናችሁ የምክር አገልግሎት መስጠት ትችላላችሁ” ብለው ፈቀዱላቸው ፡፡ ለማንኛውም አመች ሆኖ የተገኘው መኝታ ቤታችው ስለሆነ ፕሮግራም በማውጣት መጥፎ ጠባይ የነበራቸውንና ያስቸግሩ የነበሩትን ከመኳንንት ልጆች እንደነ ጃራ መሥፍንና ስለሺ በዛብህ ያሉትንና ሌሎች አስቸጋሪ የነበሩትን ልጆች እየተጠሩ ለስም ያህል ለጥቂት ደቂቃዎች የምክር አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡

ይሁን እንጂ ረዘም ያለውን ሰዓት እየወሰዱየሚመካከሩትናየሚያጠኑት ድብቅ የነበረውን ዐላማቸውን እያስፋፉ የነበሩትን ኢየሱሳውያንን ከኢትዮጵያ ለማባረር የሚችሉበትን ዘዴ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ዓላማቸውን የሚያሳኩበት ጥናት እያካሄዱ በሚደንቅና በማይታመን ሁኔታ ዓላማቸውን ካስረዷቸውና አዝነው ሃሳባቸውን የተቀበሉዋቸው በዚያን ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር የነበሩትን አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ እንዲሁም አባ መልዕክቱ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስተ ብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛ ፓትርያርክ የሆኑትን እና ሌሎችን በማሳመንና ስለ ኢየሱሳውያን ታሪክ አጥርተው የሚያውቁትን  በሌሎች ሃገሮች እምነታቸውን ለማስፋፋት መንግሥት እሰከመገልበጥ ደረጃ እንደሚደርሱ በመግለጥ ከፍተኛ ሥራ የሰሩላቸውን በወቅቱ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልዩ ጽሕፈት ቤት ያገለግሉ የነበሩትንና አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩትን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሕንዳዊውን ሚስተር ፓል በርጊስ የማህበሩ አባላት እንዲሆኑ በማድረግ ማኅበራቸውን አጠናክረው ዓላማቸውን ማሳካት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ፡፡

በትምህርት ቤቱ መኝታ ቤታቸው ለስም ያህል ለተማሪዎች የምክር አገልግሎት እንሰጣለን በሚል ይሰብሰቡ እንጂ ዋናው ስብሰባ ግን እሑድ እሑድ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ ውስጥ በምዕራብ በር ሲገባ በግራ በኩል በሚገኘው አባ መልእክቱ( በኋላ አቡነ ቴዎፍሎስ )በሰጡአቸው ድብቅ የስብሰባ ቤት ነበር፡፡

ማኅበሩ ከዓመት በላይ ጥናቱን ሲያካሄድ ቆይቶ አጠናቀቀና ጉዳዩን በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለመግለጥና ሊቃውንቱ እንዲሰበሰቡላቸው ለመጠየቅ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ ይኖሩ ወደነበሩት የእጨጌ ገብረጊዮርጊስ በኋላ አቡነ ባስልዮስ ተብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትርያርክ ዘንድ ሄደው ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡ በዚያን ወቅት አጋጣሚ ሆኖ እሳቸው ከነ ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ ጋር ስለ ጳጳሳት ሹመት ለመነጋገር ወደ አሌክሳንድሪያ ለመሄድ ተነስተው ስለነበረ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ቢሰሙ ስለሚያዝኑና አደገኛም ስለሚሆን በአባ መልዕክቱ ሰብሳቢነት መጀመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ሊቃውንት ብቻ በምስጢር ተሰብስበው በሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ “በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሊቃውንት ይሰብሰቡልን” የሚለውን ሐሳባቸውን ለጊዜው እንዲተው ለምነው ና አግባብተውእንዲስማሙ ተደረገ፡፡

ገብረጊዮዎርጊስ ጋር በተስማሙት መሠረት፤ እሳቸው ወደ አሌክሳንደርያ ሄዱና በአባ መልዕክቱ ሰብሳቢነት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ሊቃውንት በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በምዕራብ በኩል በሚያስገባው በር ላይ በግራ በኩል ባለው እስካሁን በሚገኘው አዳራሽ ውስጥ እጅግ ስሜታዊ የሆነ ና በሐዋርያት መልክ በአስራ ሁለት አባላት የተሰባሰቡትን ማኅበርተኞች ጉባኤተኞቹና የአዲስ አበባ ሊቃውንቱን ሁሉ እንባ ያራጨ ስብሰባ ተካሄደ፡፡

በዚህ በድንገት በተከሰተ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እዚህ በአዲስ አበባ  ከተማ በሚገኙት ገዳማትና አድባራት የሊቃውንት ጉባኤ በኋላ የማኅበሩ ምስጢር እየሾለከ ወጣና አንዳንድቀንደኛ የማኅበሩ አባላት ናቸው ተብለው በተጠረጠሩት ላይ ምክንያት እየተፈለገ ከትምሀርት ቤት እንዲወጡ ሌሎቹም ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እዲዛወሩ ሲደረግ ከተባረሩት ተማሪዎች ውስጥ አንዱና  የመጀመሪያው ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ ሆኑ፡፡ ሆኖም፤ የትምህርት ጊዜያቸው ዐንድ ዓመት ወደ ኋላ ቢጓተትባቸውምቀደም ሲል ዐላማቸውን በመረዳት የማኅበሩ አባል ያደረጉአቸውን  የዚያን ጊዜው የትምህርት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ. ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ስለአስገቧቸው ከዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡

ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ወደ ሌሎች ትምሀርት ቤቶች እንዲዛወሩ የተደረጉትና የተባረሩትም በአቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ዕርዳታ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲገቡ ስለተደረጉ፣ ማኅበሩ በድብቅ ስብሰባውን ማካሄዱን መቀጠል ብቻ ሳይሆን፤ በየትምህርት ቤቱ የተበተኑት በያሉበት ቅርንጫፍ ማኅበር ስላቋቋሙ ማኅበሩ ተጠናክሮ ዋናውን ሚስጢር ለሰፊው የተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተማሪዎች ሳይገልጹ በደፈናው አስተማሪዎች የተማሪዎችን መብት አያከብሩም፤ ለሃይማኖት ወገኖቻቸው ያደላሉ፤ ወዘተ በሚሉ ተልካሻ ምክንያቶች በጄዙዊቶቹ አስተማሪዎችና በሚደግፉዋቸው ተማሪዎች ላይ አድማ እንዲቀሰቅሱ ተደረገና ከፍተኛ ብጥብጥ ተነስቶ ትምህርት ቤቱን ማስተማሩን ከማቋረጥ ደረጃ ላይ አደረሰው፡፡

ይህንን ጊዜ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ስለተደረገው ከፍተኛ ረብሻ ከኅቡዕ ማኅበሩ አባላትውጪ ትክክለኛ ምክንያቱን የሚያውቅ አልነበረም ፡፡ዶ/ር አክሊሉ ኃብቴም ለዚሁ ጥናት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ጉዳዩ የሃይማኖት እነደነበር ተቃውሞውንም ይመሩት የነበረው የዚሁ ኅቡዕ ማህበር አባላት እንደነበሩ በስም በመጥቀስ አረጋግጠዋል፡፡ መምህራኖቹ በአደባባይ አንዳችም የኃይማኖት ትምህርት የማይሰጡ ሲሆን እንዲያዉም በተቃራኒው ሁሉም ተማሪ በሚያምንበት ቤተ እምነት እንዲሔድ ያበረታቱ እነደነበር ነገር ግን አንዳንድ ተማሪዎችን  በመነጠል በግልይሰበኩ እንደነበር ዶ/ር አክሊሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

ኢንጅነር ታደለ ብጡል መጽሓፈ ውይይት ከከበደ ሚካኤል ጋር በሚል በጻፉት መጽሓፍ በወቅቱ የተነሳውን ረብሻ ምክንያቱን ያውቁ እንደሆነ ለከበደ ሚካኤል አቅርበው ከበደ ሚካኤልም እንደማያውቁና ረብሻው ግን ንጉሠ ነገሥቱን እስከመያዝ የደረሰ የመረረ ተቃውሞ እንደነበር ጃንሆይም እንዳይመጡ የትምህርት ቤቱ ዴሪክተር ሚ/ር ዙፌል  እንደጠየቃቸው ተናግረው በተሳትፎው ውስጥ እነ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም እንደነበሩበት ገልጸዋል፡፡ፕሮፌሰር መሥፍን  በወቅቱ ስለነበረው ረብሻ ና ተማሪዎቹ ያነሱት ጥያቄ መምህራኖቹ አባቶቻችንን ሰደቡብን የሚል ነበር ሲሉ በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ጠቅሰውታል፡፡

ይህንን ተቃውሞና ረብሻ በመጀመሪያ ባለሥልጣኖች አድማውን ለማብረድ ሞክረው ስላቃታቸው ሌላው ቀርቶ ከቤተ መንግሥት አባ ሐና ጂማና የዕልፍኝ አስከልካዮች ወደ ትምህርት ቤቱ እየሄዱ አድማውን ለማብረድ ሞክረው ስለተሳናቸው፤ ንጉሠነገሥቱ ራሳቸው ወደ ትምህርት ቤቱሄዱ ሲሉ የሚገልጹት ደጃዝማች አድማውን ለማብረድ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተገኝተው የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ሌት ከቀን ሲጥሩ፤ ተማሪዎች ምኞታቸውን የሚያሰናክል ችግር በመፍጠራቸው ተበሳጭተው ስለነበረ፤ ለንጉሠ ነገሥቱ የአድማውን ምክንያት ለማስረዳት ከሞከሩት ውስጥ አንዱ ተማሪ ዮሐንስ መንክር ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርቦ ሲናገር፤ ንጉሠ ነገሥቱ ተናደው በጥፊ ሲመቱት ሌላውን ያልተመታውን ሁለተኛውን ጉንጩን አመቻችቶ ስላቀረበላቸው ሊመቱት የቃጡበትን እጃቸውን እንደመለሱ እስካሁን እንደ ተረት ሆኖ የሚነገር ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህ ሲሆን በዚያን ጊዜ ደጃዝማች ኮተቤ ቀ.ኃ.ሥ. ሁለተኛ ደረጃ ይማሩስለነበር ተማሪዎች ባነሱት ከባድ ረብሻ ወቅት የሆነውን በትክክል ባያውቁትም እንደተከታተሉት ከሆነ አድማው እንደተረጋጋ ጥቂት ተማሪዎች ወደጠቅላይ ግዛቱና አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኙ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ሳይባረሩ አልቀሩምብለዋል፡፡

Scroll to Top