ወንጌል፡- ዮሐ. ፭፥፩-፲፯
‹‹ከዚኽም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲኽ ኾነ፡- ጌታ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፣ በኢየሩሳሌም ድኅነት የሚገኝባት መጠመቂያጥ ነበረች፡፡ ስሞዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል የበጎች መዋኛ ማለት ነው፡፡ አምስት እርከኖች ነበሩአት፣ ከዚያም ብዙ ድውያን፣ እውሮች፣ አንካሶች የሰለሉ፣ የደረቁ፣ እግረ አባጦች፣ ልምሾች ተኝተው የውኃውን መታወክ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃውም መታወክ በኋላ መጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ኹሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ ከዚያም ከታመመ ሰላሳ ስምንት ዓመት የኾነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም ያን ሰው ከአልጋው ተጣብቆ ዐየና በደዌ ታስሮ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ ልትድን ትወዳለኽን አለው፡፡ ድውዩም አዎን ጌታዬ ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜም ሌላውም ቀድሞኝ ይወርዳል አለው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ተነሥና አልጋኽን ተሸክመኽ ሂድ አለው፡፡ ያን ጊዜም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያቺ ቀንም ቅዳሜ ነበረች፤ አይሁድም የዳነውን ሰው ዛሬ ሰንበት ነው አልጋኽን ልትሸከም አይገባኽም አሉት፡፡ ርሱም መልሶ ያዳነኝ ርሱ፤ አልጋኽን ተሸክመኽ ሂድ አለኝ አላቸው፡፡ አይሁድም አልጋኽን ተሸክመኽ ሂድ ያለኽ ሰውዬው ማነው ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ኾነ ዐላወቀም፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበረበት በብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፤ ከዚኽም በኋላ ጌታ ኢየሱስ ያን ያዳነውን ሰው በምኩራብ አገኘው፡፡ እነኾ! ድነሃል ግን ከዚኽ የባሰ እንዳያገኝኽ ዳግመኛ እንዳትበድል ዕወቅ አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታ ኢየሱስ እንደ ኾነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚኽ አይሁድ ጌታ ኢየሱስን ያሳድዱት ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲኽ ያደርግ ነበርና፡፡››
ዋና መልእክት
•እግዚአብሔር ሕሙማንን በምሕረቱ ይጎበኛቸዋል፡፡ ከደዌአቸውም ፈውሶ ጤንነታቸውን ሊመልስላቸው ይችላል፡፡
•እግዚአብሔር በደዌያት ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ያለውጣ ውረድ ያድናል፣ የዳነ ሰውም አዳኙን ማወቅ፣ ውለታውን በደግ መመለስ ይገባል፡፡
ተጨማሪ መልእክት፡-
•ሰው በደረሰበት ችግር ላይ የባሰ ችግር እንዳያጋጥመው እግዚአብሔርን ማሰብ ይገባዋል፡፡ ኅብረተ ሰቡም ምንም ምክንያት ሳያደርግ በሽተኞችን ለመርዳት በጋራ መወያየት ይገባዋል፡
‹‹ ሰዎችም በአልጋ ተሸክመው ልምሻ የኾነ ሰው አመጡ፤… ጣራውን አፈረሱና ከነ አልጋው ወደ ቤቱ ውስጥ አውርደው በጌታ ፊት አኖሩት፡፡››
ሉቃ.፲፰-፳፩፣ ፊል.፪.፫
/መዝሙር ዘመጻጉዕ አምላኩሰ ለአዳም/
ገላ.፭፥፩
ያዕ.፭፥፲፬
የሐ.ሥ ፫፥፩-፲፪
ምስባክ፡-መዝ ፵፥፫
እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ
ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቢሁ እምደዌሁ
አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ
ትርጉም፡-
እግዚአብሔር ከታመመበት አልጋ ሳለ ይረዳዋል
መኝታውን ኹሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፡፡
እኔስ አቤቱ ይቅር በለኝ እላለኁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ለዓለመ ዓለም አሜን!!!
ምንጭ
ቃለ ሕይወት፤ ሊቀ ትጉኀን ኀይለ ጊዮርጊስ ዳኘ
ሰባቱ አጽዋማት፤ ተስፋዬ ምትኩ

