” ብፁዕ ዘይሁብ እምዘ ይነሥእ- ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው ” የሐዋ. ሥራ ፳፥፴፭

 

    ⛪️ ተቀዳሚ ሐሳብ ንኡ ንሑር ወንኡ ንሁብ ኑ  ለመስጠት  እንሂድ
ዐዕማደ ሃይማኖት የአምልኮ መገለጫዎች በጌታችን በመድኃኒታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ስብከት የተገለጡት አንቀጸ ብፁዓን ናቸው።
ከቅዱሳን አባቶቻችን እንደ ተማርነው ወደ ሰማይ መጥቆ ቁልቁል የሚመለከት ንሥር ኹሉን መመልከት  እንዲችል ኹሉ ጸሎትም የተሰወረውን መመልከቻ መነጽር ነው። ታዲያ ንሥር አንዱ ክንፉ ከተሰበረ መብረር እንደማይችል ኹሉ ከጾም እና ከምጽዋት የተለየ ጸሎት በራሱ ብቻ ሊቆም አይችልም።

ስንመጸውት እግዚአብሔር የዋለልንን ውለታ እያሰብን የተቀበልነውን መክፈላችንን ልብ እንላለን፤ ቅዱስ ጳውሎስ  ይኽንን ቃል ሲያጸናው  < < ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ እንዲኽ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያስቸዋልና >> ዕብ. ፲፫፥፲፮

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ብፁዕ የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ እናያለን (በተለይም በብሉይ ኪዳን) ።  በሐዲስ ኪዳንም አምላካችን በተራራው ስብከቱ ላይ ብፁዓን . . . እያለ ሲያስተምር። ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት እንዲኹም ስለ በጎ ሥራው ሰው እንደሚመሰገን ያስገነዝበናል።

ብፁዕ  ” ευλογημένος- Makarios” የሚለው ቃል ትርጉም በመዝገበ ቃላት ፍቺ ላይ በቁሙ የተመሰገነ የታመነ ሥራው እና ልቡ የቀና የተከናወነ ክቡር ምስጉን ምሩቅ ቸር ብእሴ እግዚአብሔር እንደ ኢዮብ እንደ አብርሃም ያለ  ይለዋል ።
በመኾኑም ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የተመሰገነ የተወደደ ቸር ነው ብለን መፍታት እንችላለን።

በእምነት ወደ ርሱ ለሚቀርቡ አማንያን የኾኑ እና ያልኾኑትም ጭምር የይቅርታውን በር ከፍቶላቸዋል። ስለ ጸሎቱ እና በጎ ምጽዋቱ የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ያገኘውን በረከት በምሳሌ ማየት ይቻላል። የእግዚአብሔር መልአክ ለቆርኔሌዎስ ተገልጦ ” እነኾ ጸሎትኽ እና ምጽዋትኽ በእግዚአብሔር ፊት ደረሰ ” የሚል የምሥራች ነገረው ቅዱስ ጴጥሮስን ወደ ርሱ ልኮ አጠመቀውም። ሐዋ.፲፥፫-፬

መስጠት ታላቅና የከበረ የመንፈስ ፍሬ  መኾኑን እና ከኹሉ የበለጠ ክብር በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጦታል። “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል። በጎነቱም መልሶ ይከፍለዋል።” ምሳ. 1።፲፱፥፲፯
  ቅዱስ ባስልዮስ ” በጎ የማታደርጉ ሰዎች እናንተም ምሕረትን አታገኙም፤ እናተም በነዳያን ላይ በራችኹን እንደ ዘጋችኁ ኢየሱስ ክርቶስም የዘለዓለም ሕይወት እንዲሰጣችኁ በለመናችኹት ጊዜ ፈጽሞ አይሰማችኹም ” ይለናል።

በረከተ ምጽዋት (ከመንግሥተ ሰማያት ተጨማሪ የሚሰጠን ንኡሳን በረከቶች)
 
 🍇 ከኃጢአት ለመጠበቅ ያዘጋጃል ፦ ነቢዩ ዳዊት ከመዝሙራቱ አንዱ ” ለችግረኛ እና ለምስጉን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋልና ” መዝ. ፵፥፩

🍇 ውስጣዊ እርካታን እና ደስታን እናገኝበታለን ፈላስፋው “ለራሱ የሚኖር ሰው በሌሎች ሊከብር አይችልም ” በማለት የመስጠትን ጥቅም ይነግረናል።

 🌟አንድ ታሪክ እናንሣ አንድ ሰው ለሦስት ጓደኞቹ ንጉሥ ጋር ተጠርቼ ልሄድ ነው አላቸው። አንደኛው ጓደኛው እኔ እስከ መንገድ እኩሌታው አብሬኽ እሄዳለኁ አለው። ኹለተኛው እኔ እስከ ቤተ መንግሥት አብሬኽ እሄዳለኁ አለው ።
ሦስተኛው እኔ እስከ ቤተ መንግስት አብሬኽ እሄዳለኁ ንጉሥን እንድታገኝ እረዳሃለኁ ብትከሰስም ጥብቅና እቆምልሃለኁ አለው። እነዚኽ ወዳጆቹ  አንደኛው ምናኔ ኹለተኛው ድንግልና እና ሦስተኛው ምጽዋት ናቸው። ምጽዋት ከእግዚአብሔር እልፍኝ ገብታ ጥብቅና የምትቆም ናትና።

 ✍️ እግዚአብሔር ለኛ እንደ ሰጠን እኛም ስለ እግዚአብሔር ብለን ፍሡሕ በኾነ ልብ ብሩህ በኾነ ዐይን ለጋስ በኾነ እጅ ለድኾች እንመጽውት። ” ደስ ብሎት የሚሰጥን ሰው እግዚአብሔር ይወደዋል፣ከንቱ የኾነ ንፍገቱን ግን ይጠላል፤ ለድኻ የሚመጸውት ሰው መመጽወቱ መብላቱ ነው እንጀራውን ለጦም አዳሪዎች ሰጧልና” ምሳ. ፳፪፥፱

🌟እጅግ የሚያስገርመው ነገር በመጽሐፈ ቅዳሴ ላይ ካህኑ የሐዋርያትን የመባዕ ጸሎት ሲያደርግ ” ይሰጡ ዘንድ ሲወዱ የሚሰጡት ከሌላቸው ላይ ፈቃዳቸውን ተቀብሎ መንግሥተ ሰማያትን ይሰጥ ዘንድ . . .  ” ይላል የምንሰጠው ባይኖር እንኳን ፈቃዳችንን ይመለከታልና ነው። ተመልክቶም ከሰጡ እኩል ያስብልናል። ለሰጡት የሚሰጠውን ይሰጠንማል።
ስለዚኽ ኑ አብረን ሄደን ወገኖቻችንን እንጎብኛቸው።

እግዚአብሔር አምላክ ምጽዋታችንን ይቀበለን !!!
✍️በዲ/ን ዶ/ር  ቴዎድሮስ ለገሰ
    የካቲት 2015 ዓ.ም

Scroll to Top