አበበ ከበደ የተምሮ ማስተማር አዳም(፲፱፻፳፬-፲፱፻፸፩)፤፤

(ሥመ ክርስትና ገብረኪዳን፤፤)

አቶ አበበ ከበደ(ገብረ ኪዳን) ከህይወት ታሪካቸው የዚህ ጥናት አቅራቢ እንደተረዳው ከስመ ጥሩ አርበኛ ከፊታውራሪ ከበደ ወልደ ጊዮርጊስና ከወ/ሮ ዐመለወርቅ ኢየሱስ በ፲፱፻፳፬ ዓ/ም አርሲ ክ/ ሀገር ተወለዱ፡፡

እንደ ብዙዎች ልጆች ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ን.ነ ዘኢት. የአርበኛ አባታቸውን ውለታ በማስታወስ በቀድሞው ተፈሪ መኰንን ት/ቤት በአዳሪነት እንዲማሩ አደረጉ፡፡ በዚሁ ት/ቤት እስከ ፲፱፻፵፫ ዓ/ም ድረስ ተምረዋል፡፡በ፲፱፻፵፬ ሐረር መመህራን ማሠልጠኛ ት/ቤት ገብተው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ ቀ.ኃ.ሥ ኮከበ ጽባሕ ይባል በነበረው ት/ቤት ተመድበው ሲያስተምሩ ባሳዩት ችሎታና ቅን አገልግሎት ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው ወደ አሜሪካ በመሔድ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር ውሰጥ ተመድበው በመጀመሪያ የዕደ ጥበብ ማዕከል ኃላፊ ቀጥሎም የአሁኑ ብሔራዊ ቴያትር (የቀድሞው የቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር) ዲሬክተር በመሆንም አገልግለዋል፡ ኃላፊነታቸውን በሚያስመሰግን ሁኔታ በመወጣታቸው በለንደንየትምህርት አታሼ ሆነው ተሾሙዋል ፡፡ በዚህም ኃላፊነታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ አበይት ተግባራትን በማቀድና በማከናወን ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እንዳበረከቱ ታውቋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በመጀመሪያ ኢየሱሳውያን በመባል የሚታወቁትን የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መምሕራን የሚያደርጉትን ቅሰጣ በጽኑ በመቃወም የተማሪውን ተቃውሞ መርተዋል፡፡ ደጃዝማች ስለ አበበ ከበደ  ሲገልጹ ከሁላችንም በጣም ልጅ እርሱ ነበረ፡፡መንፈስ ቅዱስ የቀረበው የሚሠራው ሁሉ የሚሳካለት ተምሮ ማሰተማርን በመመስረት ቀዳሚው ሰው ነበር ከታደሰ መንግስቱ ጋርም የቀረቡ ጓደኛሞች ነበሩ ይላሉ፡፡

ኘሮፎሰር መስፍን ወልደማርያም ሥልጣን ባህልና አገዛዝ ፖለቲካና ምርጫ በሚል በ፳፻፫ ዓ.ም ባሳተሙት መፅሐፈ አበበ ከበደን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቀርብ ጓደኛዬ ነበር በጣም ርኅሩኅና ሃይማኖተኛ ሰው ነበር ብለው ከስር በኅዳግ አበበ ሁሌም በበጎ አድራጐት ሥራ ላይ አካል ጉዳተኞችንና ደሀዎችን ለመርዳት ሲጥር የነበረ ሰው ነው ከነደጃዝማች ካሣ ወልደ ማርያምና ከነ አቡነ ቴዎፍሎስ ጋር በደርግ የተገደለ ነው ብለዋል፡፡ዶ/ር አክሊሉ እኔ እስከ ማስታውሰው አበበ ከበደ ማህበሩን ለመመስረት በዋናነት ወዲያ ወዲህ ከሚሉት ውስጥ ሲሆን  ለኔም ስለ ማህበሩ የነገረኝ እርሱ  ነው፡፡ዘመናዊ ትምህርት ና መንፈሳዊ ትምህርት በአንድ ላይ ማስኬድ ይቻላል የሚልዘመናዊ መሆን የጥንቱን የሚያስንቅ ሳይሆን የሚያስወድድ ነው የሚል ዕምነት የነበረው ጨዋ ሰው በመንግስት ኃላፊነት እንኩዋን ሆኖ ማኅበሩን በግለሰብ ደረጃ ና በከፍተኛ ደረጃ ይከታተል ነበር ሲሉ ለዚህ ጥናት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ማህበሩን አንደመሠረቱት የሚታመኑ በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም መጀመረያ ፲፪ ሆነው ከተቋቋሙት አባላት መካከል በተለያየ ምክንያት ትምህርት ቤቱን ለቀው ሲሄዱ ፭ (፮) የሚሆኑትና ስማቸው ከዚህ በታች የተጠቀሱት ተማሪዎች በ አበበ ከበደ አሰባሳቢነት ከዚሁ ዘመናዊ ት/ቤት መከፈት ጋር በተያያዘ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ማኅበራትን መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ለተምሮ ማስተማር ማኅበር መመሥረት ጥንስስ የሆነውየተጣሉትን ማስታረቅና መፅሐፈ ቅዱስ ጥናት በሚል ሽፋን የተሰባሰበው ኅቡዕ ማኅበር ውስጥ ቀሪ አባላትን ይዘው ቀጣዩን ስራ ለመስራት ወደፊት መጓዝ ጀመሩ፡፡

በዚህም መሠረት

  • ፩ኛ አበበ ከበደ
  • ፪ኛ ታደሠ መንግሥቱ
  • ፫ኛ አቶ ሥዬም ወ/አብ
  • ፬ኛ አቶ መኮንን ዋሴ ነበሩ፡፡

መኮንን ዋሴ የሚለው ስም መስፍን ዋሴ በሚል ታደሰ መንግስቱ ጠቅሰውታል ይሁንና ደጃዝማችም ሆኑ ደ/ር አክሊሉ መኮንን ዋሴ እያሉ በመጥራት ተጠቅመዋል፡፡ የአምስትኛውን እና ስድሰተኛውን ስም ማግኘት አልተቻለም ፡፡ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት በዚህኛው ውስጥ በአባልነት የለሁበትም ብለዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው ዜና ሕይወቱ ለብፁዕ አቡነ መልከጻዲቅ በሚል በአቀነባባሪነት በፃፉት መፅሃፍ አቡነ መልከ ጻዲቅ እንደገለጹት በምስካየ ኅዙናን ቤተክርስቲያን አካባቢ በመነኮሳት ቤት ፯ ወጣቶችን በግል እየሰበሰብኩኝ አስተምር ነበር ብለው ከላይ የተጠቀሱት ፬ ሰዎች ላይ ሞገስ ብሩክ እና ወይዘሪት የሺ እመቤት እማኙ የሚባሉ ሥሞችን በመጨመር የተምሮ ማስተማር ማኅበር እንዲመሠረት እንዳደረጉ ገልፀዋል፡፡

ይሁንና ከዚህ መፅሐፍ ውጪ እነዚህ ሁለት ተጨማሪ ሥሞችን ማግኘት አልተቻለም፡፡

የ፲፱፻፴፱ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያነሱትን የሃይማኖት ቅሰጣን ተቃውሞ ተከትሎ በ ፲፱፻፵ ዓ.ም ለሁለቱም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ማለትም ለተፈሪ መኮንንና ለእቴጌ መነን ( በአሁኑ አጠራር የካቲት ፲፪ ከፍተኛ ትምህርት ቤት) ተማሪዎች ሲባል በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ቤተ ክርስትያን መሰረት ተጣለ፡፡

የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አመሠራረት በሚለው መጽሓፍ አባ ተክለ ማርያምእንደገለጹትንጉሠነገሥት ቀ.ኃ፣ሥ መሠረት በተጣለበት ቀን ባደረጉት ንግግር “…በተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ክበብ ውስጥ ይህን የአዲሱን ቤተ ክርስትያን መሠረት ሥንመሠርት በዚህ ተማሪ ቤት የሚማሩ ክርስቲያናውያን ወጣቶች የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታቸውን ሥርዓት እንዲጠብቁበት ሥርዓተ ጸሎትና ሥርዓተ ቁርባን በመፈጸም እንዲጠቀሙበት አስበን ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ይኽም የም.ኅ.መ.ገ  ከነበረበት የቀድሞው ቀ.ኃ.ሥ በአሁኑ አጠራር የካቲት ፲፪ ሆስፒታል ወቶ አሁን ባለበት ቦታ እንዲሰራ ያደረገው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ና የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በዚህ ሥፍራ መገኘትና በኅቡዕ የተማሪዎች ማኅበር በወቅቱ የተነሳው ረብሻና ተቃውሞ ላይ ባነሡት ምክንያት መሆኑ ግልጽአድርጎታል ፡፡

Scroll to Top