መንፈሳዊ-ወግ

ቅኔ – ቤቴ

ዲ/ን ናትናኤል አዲሱ

ሰማዩ ጉም ሸፍኖታል ዕፅዋት የአዲሱን ዘመን መምጣት ተከትሎ በሀሴት ይዘምራሉ፤ አዕዋፍት ለጆሮ ጣፋጭ የሆነ ዜማ በህብር ያዜማሉ ለአምላክ የሚቀኙት ውብ ቅኔ ከወዲያ ወዲህ ይሾራል፡፡ ወንዞቹን እያፏጩ በረአድ የሚያስገመግማቸው ድፍርስ ማይ የረጋ ፍኖቱን ከጀመረ ሶስት መዐልት በነግ መሰየሙ ነው፡፡ ሠማዩን በምልዐት ሸፍኖት የቆየው ጉም በስሱ ማንጠባጠብ ጀምሮል፡፡

‹‹…ጋሽ ዮነስ›› ‹‹አቤት›› ‹‹ዝናቡ እያካፋ ነው ወደ ውስጥ ግቡ›› ‹‹እሺ›› እሺ ሚለውን ቃል አስቦት ከአፉ የወጣ አይደለም ለተጠየቀው ጥያቄ የሚቸረው ክርስቲያናዊ ምላሽ ነው፡፡ በስሱ የሚያን ጠባጥበው ጠል ፊቱ ሰፍፎበታል የውስጡን ስሜት ኮርኩሮ የገባው ነገር የሩቁን ዘመን ሁነት ጀባ ብሎት እንባው ይገነፍላል፡፡ ፊቱ ዛሬ የደስታ ዕንባ ከትሞበታል ዕንባው ይደነፋል፡፡ ‹‹ ጋሽዬ ዝናቡ ሳይበረታ ወደ ውስጥ አይዘልቁም?›› ቤቱን በኃላፊነት ተረክባ የምትመራው እንስት ፋኖሴ ጥሪ ነው፡፡ ዮናስ ግን አይመልስም ዝም…ዝም…ዝም… በቃ ፡፡ ግስሙ ክንፍ አውጥቶ መብረር ቃጣው የዘመንን መቀነት ስቦ በትዝታው ፈረስ ላይ ረቦ ከወጣትነቱ ዘመን ደረሰ፡፡ ዐርባ ዐመታት የኋሊት አማትሮ ዘለቃቸው፡፡

‹አሐደ›

መኸርና በልግ ተዳፍኖ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቷል፤ረኃብ እያላወሰ ከመቃብር የሚዶላቸው ሕፃናት ታላቅ ኀዘን ይጭራሉ፡፡ ዋይታ በዝቷል ጮኸ የሚያለቅስ የለም፤ በምን አንጀቱ የመንደሩ አስለቃሽየነበረችው ዓለሚቱም ካልጋ ከዋለች መንፈቅ ሞልቷታል፡፡ ደጋው ነዋሪ ማኅበረሰቡም ልጁን እያንጠለጠለ ወደ ከተማ ይሮጣል፡፡ በከተማም ያለው ህዝባዊ ዓመፅ ተቀጣጥሏል ማንም ድርቁና ረኃቡ ስለሚፈጃቸው ጨቅላ ሕፃናት የተቆረቆረ የለም፡፡ አዲስ አበባ በአብዮት ታምሳለች ከሸገር የሚነፍሰው የጥንቱ መልካም ነፋስ አዲስ አበባይቱን ኮረዳ በአርምሞ ሰቅዟታል፤ ውቤ በረሃም ውኃ ጽም አድሮቆታል፡፡ ድምጽ የለም ዝ.ም.ም… ምሁሩ ቀፀለ ‹አብዮት የሰው ልጅ የገነባውን የሕይወት ድር ከመበጣጠሱም በላይ ማኅበራዊ ይዘትና ቅርፅ ከያዘ መዘዙ በቀላሉ የማይቀል መርዝ ነው፡፡ በአብዮቱ መንፈስ የተመረዘ ኅብረተሰብም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮው ድርና ማግ እየተሸማቀቀ ወደ ድህነት ማዘቅዘቁ አይቀሬ ነው…›› የአብዮታዊው ጎራ ጽንፈኞች ደግሞ በራሪ ወረቀቶችን ያለማቋረጥ በከተማው ያሰራጫሉ፡፡ ‹‹…ሀገር የጋራ ናት ሃይማኖት የግል ናት፡፡›› የቤተ መቅደሱ ካህናት በአንድ ላይ እኩል ይናገራሉ፡፡

ከአለቃ ዋክሹም ጌታሁን አንደበት እየተሰረቀ የሚወርደው ዝማሬ ሕሊናን ወደ አርያም ይነጥቃል፡፡›› ኢትዮጵያ ታበፅህ አደዊኅ ኀበ እግዚአብሔር …›› ቀጣዩን ስብከት የተጀመረው በዚህ መዝሙር ነው፡፡ ለጥቀውም መንፈስ ቅዱስ ያቀበላቸውን የወንጌል ቃል ያዘንቡት ጀመር ‹‹የወደፊቱ የሰው ዘር ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ዛሬ የሚከተለውን የጥፋቱ ጉዞ አርሞና አስተካክሎ ራሱን ከራሱ ጥፋት ያተርፍ ይሆን ? ወይስ በጀመረው የኃጥኣት እሽቅድድም ከጥፋቱ ጋር ይላተም ይሆን?›› ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጽቆጣጠረውን ልባዊ ደስታ ልታጎናፅፈው ይገባል ፡፡›› ልቡ በሃይማኖት ፍቅር የተቃጠለ ወጣት የተናገረው ንግግር ነበር፡፡ ‹‹አዎን›› አሉ አለቃ ለጠቁ ‹‹ሀገራችን የሚተናነቃት ችግር ሊፈታና ዘላቂ ሰላም ሊገኝ የሚችለው ፍጹም የሆነ ሀቀኝነትና መተሳሰብ የተጨመረበት እንደሆነ ነው፡፡  ሕዝብ ሆይ !ለዓለም የምንመኘው ምንድን ነው? የእግዚአብሔርን ብርሃን ወይስ የተድበዘበዘ የስልጣኔ ብልጭታ እ…›› በየአድባራቱና ገዳማቱ ሁሉ ሕዝቡ ባንድነት ለጸሎት ተሰልፏል፡፡ ‹‹አምላክ ሆይ !ኢትዮጵያን ከተረገጠባት ችግር አድናት፡፡›› አለቃው ፈጽሙ አሜን፡፡ ከወዳኛው ጽንፍ አስተጋባ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!›› አሜን፡፡

ወደ እነ ዮናስ መንደር ልመልሳችሁ፡፡ ዐፅመ- ታሪኩ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ዮናስ አሁን የአስራ አምስት ዓመት ልጅ ነው ፡፡ ከአባቱ ከአቶ የኋላሸት አስማማውና ከእናቱ ከወ/ሮ የዋግነሽ ስዩም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተወለደ፡፡ እጆቹ ወደ መቁጠሪያ አንደበቱ ወደ ፊደል ሲዘግር ልሳኑን ‹‹ ሀ.ሁ›› ብሎ ገራው፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ከወጣበት እለት አንስቶ ይህን መሰል መከራ አልተጋፈጠም፡፡ ረኃቡ የቆሸቆሳ ስደት ጨምሯል፡፡ ደመናው ሲያደምን አምላክ ተታረቀን ሲሉ አያ ነፋስ ነጥቆ ከከተሜው ይዶለዋል፡፡ ለከተሜው ዝናብ ምን ሊበጅ›› ይላሉ ‹‹ለችግር የጣፈን››ተስፋቸው ተሟጧል፡፡ምድሪቱ ዕለት ዕለት በአቧራ ትታጠናለች፡፡ የእነ ዮናስ ጨቅላ ጓደኞችም ወደ መጡበት ዓለም እየተጠሩ ነው፡፡ ከሞት ከተረፉት አምስት የዕድሜ አቻዎቹ ጋር ማታ በስፋት ሲያውጠነጥኑት የነበረውን ሐሳብ በልባቸው ሸክፈው፣ላመል የተረፈቻውን ታዛ መሸሻ ባኒ ተካፍለው ‹‹ደኅና እደር›› ‹‹ደህና እደር›› ተባባሉ፡፡እርጅና ያደከማቸውን እናቱንና አባቱን የምትደግፋቸው እህቱ ናት፡፡ ያደጉበትን ማኅበረሰብ እና እምነት ጥለው ወደ አዲስ ባህልና እምነት ጎራ ሊሉ፣ ቅኔ ቤታቸውን ጥለዋት ሊሄዱ ነው ያደጉበትን የእምነት ቀዬ ጥለዋት ሊኮበልሉ የሚጠባበቁት የሌቱን መንጋት ብቻ ነው፡፡ ይህች የቆሎ ቤት ለኅብረተሰቡ ባለውለታ ነች፡፡ እለት እለት የኃያሉ ጌታ የመድኀኔዐለም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት የጻድቃን ሰማዕታት ምስጋና ይዘንብበታል ዙሪያዋ በቅኔ የቀለመ በአምላክ በረከት፣ በፅኑዕ አምድ የፀናች ቤት ናት፡፡ በሌት በቅኔ ትደምቃች በዜማ ትወዛለች፡፡ እልፍ ሊቃውንት ይፈሩባታል፡፡ ዛሬ ግን ለዚች በጎና ባለ ውለታ እናት መርዶ ተደገሶላታል፡፡ አፍላ ዲያቆናቷ ጥለዋት ሊሸሹ ነው፡፡ ይህን ስውር ሴራ ያደራጀው አንድ የአውሮፓ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ ድርቅና ረኃቡ ምቹ ጊዜና ቦታን አመቻችቶላቸዋል፡፡

ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከገቡ ሰልስታቸው ገደፈ፡፡ በረብ የለሽ ስራቸው ግን ዕርዳታው እየተጓተተ ነው፡፡ ይህችን ቤተ እግዚአብሔር፣ ቤተ ሊቃወንት፣ ቤተ ማርያምን በኀዘን ሊያናውጿት ነው፡፡ ወፎች መንጫጫት ሲጀምሩ ዮናስ ፣ክፍሌ፣ ጌታቸው፣ተክሌና ፍልሰቱን የሚመራው የቅኔ ተማሪ ሌት እንቅልፍ ነስቷቸው የነበረው ጉዳይ ቀስቀሳቸው፡፡ በሁሉም ልብ አዲስ አበባ ተስላለች፤ አዲስ አበባ ስላለው ችግር ማን ገልጦ ነግሯቸው፡፡ ከተቀጣጠሩበት ግራር ዛፍ ስር ተገናኙ፡፡ አንድ ሰው ግን ቀርቷል የዓስራ አምስት ኣመቱ ሁሉም ተሸበሩ ዓስራ ሁለት ሰዓት ሊሆን ሰቂቃዎች ብቻ ቀርተዋል፡፡ ጊዜው እየነጎደ ነው፡፡ ኋላ የቅኔ ቤቷ ተማሪዎች ከመጡ ትልማቸው መስተጓጎሉም አይደል በመጨረሻ መጣ፡፡ ተክሌ የርግማን ስንቅ አስታጠቀው፡፡ ክፍሌ ደግሞ በነገር ይወጋው ጀመር ሁሉም አለፈ፡፡ አምስት ሆነው ከጠባቡ ጋራ አንዱ ባንድ ላይ ተጫኑ በሁሉም ህሊና አዲስ አበባ ተቀርፃለች፡፡

‹‹ከሁለት ቀን በኋላ አዲስ አበባ እንደርሳለን ጠንከር ማለት ነው፡፡›› አለ ተክሌ ዮናስ ተሸብሯል፤ ሁለት ልብ ሆኗል፡፡ የቅድስት ቤታቸውን አነርሱ በምትፈልግበት የመከራ ወራት ልጆቿጥለዋት ኮበለሉ፡፡ በዮናስ ህሊና የኔታ ከተፍ አሉ ድንጋጤ ቢጤ ከእንቅልፉ አባተተው፡፡

ዓይናቸው ቢታወርም በነግ ሐዲስ ተስፋን አንግበዋል፡፡ ሊቅ የማፍራት ህልማቸው ከቶ አልነጠፈም፡፡ ረኃብ ሰቅዞ ይዟቸው ስንኳ ሸጥና ዱሩን እያሳበሩ ይመጣሉ፡፡ ‹‹የኔታ …›› ባለጋሪው ከታዘዘበት አድርሷቸው አቅንቶ ተመመ፡፡ ቅኔ ቤቷ ተሸብራለች፡፡ ከወትሮው ሰራዊቶቿ በቁጥር አንሰዋል፡፡ የኔታ ተጨንቀዋል፣ እነርሱን ፍለጋ ያልተላከ ሰራዊት የለም፡፡ መልእክተኞቹ የፍልሰታቸውን ወሬ ይዘው መጣ፡፡ ‹‹የኔታ ወደ ሸዋ ሄደዋል›› የኔታ መቼ አምነው ልባቸው ደማ አነባ፡፡ ከእናታቸው እቅፍ ተቀብለው ለቁም ነገር ያበቋቸው ዲያቆናት፣የቅኔ ቤቷ ድምቀቶች በቅኔ ሳይጎለምሱ መክሊት ብድራታቸውን ከመሬት ቀብረው ነጎዱ፡፡ ‹‹ይህች የቅኔ ቤት በልጅ ልጆቻቸው ሳይቀር ትፈርዳለች›› የዮናስ ልብ ጓደኛ የነበረው ጌድዮን ንግግር ነበር፡፡ የዘመመችው ጎጆ ሳትቃና፣ ሳንቃዋ በወጉ ሳይበጅ በቅጥ ሳትማገር፣ ጥለዋት ኮበለሉ፡፡ ‹ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኃዘን ነው፡፡ ከሀዲ ልጅ እናቱን ይንቃል መች ይረባታል አሉ የኔታ ኃዘን ባሰለለው ድምፃቸው፡፡ ለዘላለም ከቅኔ ቤቷ ማሕደር ተሰረዙ፡፡

ከፍተኛ የሞተር ድምፅ የምታወጣው አውሮፓዊት መኪና እየተንደቀደቀች መጣች ‹‹ዌልካም›› አለ ሾፌሩ፡፡ ሀገርኛ ሰላምታ ሰጥተውት ወደ መኪናይቱ ውስጥ ገቡ ከሚነጉዱበት የመኪና መንገድ በስተቀኝ በኩል በግርማ የቆመው ተራራ የታዘበው መሰለው፣ የዛሬን አያድረገውና በደጉ ጊዜ ሕፃናት በደስታ ይንቦራቹበት የነበረው መስክና ምንጭ ከዓይናቸው ራቀ የእትብታቸው መንደር በተራራው ተዋጠች፡፡እያቃሰተች ቁልቁል የምትትመው መኪና ሸኖ ገብታ አደረች፡፡ መክሊት ለገንዘብ ተሸጠች፡፡

‹‹ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ፡፡››

ከረፋዱ አራት ሰዓት ሲል አዲስ አበባ አውቶብስ ተራ ደረሱ፡፡ የሠው ብዛት፣እንደ ገልዐድ በግ ርማ የቆሙት ረጃጅም ፎቆች፣ በየሱቆቹ የቆሙተረ የማይንቀሳቀሱ ፊተ ነጭ ሰዎች፡፡ ‹‹ሎቱ ስብሐት›› መዲናዋን ሳይጠግቧት ቀበናን አልፈው የአሁኑ ‹ብሪትሽ ኢምባሲ› ካለበት አካባቢ ወደ ግራ ተገን ጥለው ካንድ ለምለም ግቢ ገቡ ‹ዶክ.ቻሪቲ› የሚለው ጽሁፍ ከመግቢያቸው ላይ አዩ፡፡ መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት ከተከራየው ግቢ ሲገቡ ሁሉ ነገር አዲስ ሆነባቸው፡፡ በውብ አበቦች የተሞላ ግቢ፡፡ በግርምት ተያዩ፡፡ ‹ሻወር ይወስዱና ለነገ ሬዲ› ይሁኑ አለ ኢትዮጵያዊው ሰው፡፡ በዚህ ግቢ ውስጥ ከፍተኛ መዓረግ ያለው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የከተማውን የአኗኗር ዘይቤ ቀስ በቀስ ተላመዱት፡፡ የቆሎ ቤታቸው ትዝታ ተዳፈነ፡፡ አሁን የሶቪየትና ሃገርኛ የተዋህዶ ነቀርሳዎች ዕቅዳቸው እየሰመረ ነው፡፡ በቅድሚያ ያሰቡት እነርሱን ከቅኔ ቤቷ ማፈናቀልና ወደ ከተማ ማምጣት ነበር እርሱም ተሳካ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ልጆቹ ላይ የተቀረፀውን የተዋህዶ ፍቅር ማቀዝቀዝ፡፡ ሁለቱም ተሳክቷል አሁን የቀረው እነርሱን ወደ ባዕድ ሀገር ማሻገር ነው፡፡

‹‹መፃኤ ዕድላችሁን የምትወስኑበት ታላቅ አጋጣሚ ነው›› ይላል በ‹ቮድካ› ደነዘዘው ኃላፊ፡፡ ቀድሞም ይህ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ተብዬ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባ ነበር ከዛም አልፎ በተዋህዶ (ክርስቲያኖች መንደር የተዘራ ዓረም ነውና እንዲህ አቆጥቁጦ የተዋህዶን ልጆች በመርዙ ሳይመርዝ ሊነቀል ይገባ ነበር፡፡ ተገባላቸው ቃል ኪዳን አውሮጳን በጉጉት እንዲጠብቅ ሕሊናቸውን አማተረው፡፡ ‹ከዓርባ ስምንት ሰዓታት በኃላ አዲስ ሕይወት ትመሰርታላችሁ››የዕለት ጉርስ ያባከነው ኢትዮጵያዊ ኃላፊ ንግግር ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ዮናስ ነገሩን ሁሉ አበላሻው ‹ወላዲቴን አልኩ እኮ!› ‹‹ሆ…ሆ ወላዲቴን ስል›› ‹‹ይህ ምንጡር አለው፡፡›› ተክሌ ጠየቀ፡፡

‹አንዴ ልሳሳት እችላለሁ ሁለቴ ሶስቴ መሳሳት አልፈልግም ከግለሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ወደ ብሔራዊ የአስተሳሰብ ለውጥ መሸጋገር አለብን እያደር እየበረታ ያለውን የፖለቲካ አመፅና ነውጥ የረኃብ ችግር፣ የሀሳብ ተቃርኖ… በአማካይነት ተሰልፈን ማቆራኘት ይኖርብናል፡፡ በንዋይ ተታለን ነበር ዳግም ግን ባዕድ ሀገር ሔደን መሞት የለብንም፡፡ የኛ ተስፋ በሰማይ ነው ሀገራችን ኢየሩሳሌም ናት በሕይወታችን ሙሉ የሚፀፅተንን እኩይ ተግባር አንፈፅም ውስኑ እኔ እመለሳለሁ ተክሌ ምን ትጠብቃለህ?›› ተክሌ የተቋጠረ ፊቱን አጨፍግጎ ቀጠለ ‹‹አልሞክረውም!›› በሶቪየት ከተሞች የቆሙት ታላላቅ ሕንፃዎች፣ በአርምሞ ወጪ ወራጁን ያለመታከት የሚመለከቱት የቡቲክ አሻንጉሊቶች በዋናነት በካቶሊክ ሚሽነር አስኮላ የሚማሩትን ትምህርት፣ የተሞናደ የካቶሊክ አዳራሽ የሚሰጣቸውን ደስታ እያሰቡ በደስታ ባሕርሰጠሙ፣የተዋህዶ የቅኔ ቤት ጎጆ ኀዘን ሰቀዛት፡፡ ልጆቿን አሳድጋ ለባዶ ዳረቻቸው፡፡ ወደ ክርሚያ (ሶቪየት) ነጎዱ፡፡ ‹‹የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና፡፡ ኃጥአንን ኃጢያቱ ታጠምደዋለች፣ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል፡፡ አልተቀጣምን እርሱ ይሞታል፣ በስንፍናውም ብዛት ይስታል፡፡›› ዮናስ ተናገረ፡፡

ዐርባ ዐመታት ነጎዱ፡- ‹ንግባ እኬ ሃበ ጥንተ ነገር› ሀገሪቱ ተረጋግታለች ንፁህ አየር ይነፍሳል፣ የተዋህዶ አበባ በየቀየው አሸብርቃለች፣ የአብነት ት/ቤቶች ተስፋፍተዋል፡፡ ተራሮች ሳር ስቡን ጠገቡ፡፡ ምድር በደስታ ባሕር ሰጥማለች፡፡ ሕፃናት በደስታ ይፈነጫሉ ሸገር ሸገርን መስላለች አዲስ አበባይቱ እንደ ስሟአብባ ፈክታለች፤ዛሬ አንድ ሊቅ በክብር ሊኳል ነው፡፡ የዚህ ሊቅ ሰው መፈክር ከሬዲዮኑ ዘለቀ፡፡ ‹ይህችን ምድር ጥለን መውጣት የለብንም ችግሩን መታገስ አለብን፡፡ ተነስ ወገኔ ትጋ በፀሎትህ፣ተነሳ ወገኔ፡፡ እያደር የሚከሰተውን አብዮትና አመፅ በአማካኝነት ተሰልፈን ማቆራኘት ይኖርብናል፡፡ ፀጥ ያለ መንፈስ ትውልድን በፅኑ መሰረት ላይ ያቆማል በዓለማችን ላይ የሰው ዘር ውድቀት እያንዣበበት ይገኛል፡፡ ተፈጥሮአዊ ባሕሪው እየተቃወሰ የሰብአዊነቱን መሰረት እየለቀቀ ራሱን በራሱ እምነትና ተግባር ከማውሰሙ በፊት የተዋህዶ አበባ በየልባችን እናስርፅ›› ይህ ሰው ታላቅ አባት ነው፡፡ መምህር ዮናስ በረኃብ ጊዜ ህዝቡን አስተባብሮ ተፈጥሮ የነበረውን መከፋፈል አስታርቆታል፡፡ ከዓርባ ዓመታት በፊት ልትፈርስ የነበረችው ቤት ዛሬ በሁለት እግሯ ቆመች፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ዮናስ በወሰነው ታላቅ ውሳኔ ይህን ማዕረግ ይዟል ‹መምህር› እንለው ዘንድ ይገባል፡፡ ከረኃብና ከጦርነት ለመውጣት ከመሰሎቹ ጋር ለዓርባ ዓመታት ያላሳለሰ ጥረት አድጓል በየቀየው ቅኔ ቤትና አስኮላ እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል፡፡ አለቃ ይህን የበሰለ ፍሬያቸውን አጣጥመው አልፈዋል፡፡ከሌሎች ጓደኞቹ መካከል ግን ይህን ያይ ዘንድ የተመረጠ የለም፡፡ ሁሉም በሶቪየት በተነሳው አመፅ ተማግደዋል፡፡ ከናፍሩ ቅኔ ቤቱን አጣቅሶ የታሪኩም ምስ ተናገረ…‹ቅኔ ቤቴ ፈረደች፡፡›ይህ ዕውን ነው፡፡ የሕይወት ጉዞ ቀጥሏል ፡- ዝናቡ በስሱ ያንጠባጥባል፡፡ መምህር ዮናስ ከትዝታው ፈረስ ላይ ወረደ፡፡በክርሚያ ሶቪየት የተማገዱት የጠዋት ጤዛ ጓደኞቹን እያሰበ ዕንባው ይፈነጫል ‹አቤቱ ነፍሳቸውን በአብርሃም እቅፍ አኑረው አሜን፡፡›

‹‹ተፈፀመ››

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን፡፡

Scroll to Top