የተምሮ ማሰተማር ማኅበር የሚለውን ስያሜ

 የተምሮ ማሰተማር ማኅበር የሚለውን ሲያሜ ያወጡት አቶ ገብረጊዮርጊስ አጋዤ ከማኅበሩ አባላት ጋር

(ፎቶ ከተምሮማሰተማር ማኅበር)

   አቶ አበበ በተፈጥሮ የታደሉትን ችሎታና እውቀት በትምህርት ከቀሰሙት እውቀትና ሙያ ጋር በማዋሐድ በሃይማኖትና በቆራጥ የሥራ ወዳድነት እየታገሉ ለታረዙ ለተራቡ ለታመሙ ለደከሙና ረዳት ለሌላቸው ብርሃናቸውን ላጡና ዕጓለማውታ ወዘተ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሰው ታላቅ የግብረ ገብ ሰው እንደነበሩየህይወት ታሪካቸው ያስረዳል ፡፡አበበ ከበደ የተምሮ ማሰተማር በጎ አድራጎት የሚል ጽሕፈት ቤቱን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ያደረገ ድርጅትም መሥርተው ነበር(የተምሮ ማሰተማር ማኅበር ፋይል)

አቶ አበበ ከበደ በተፈሪ መኰንን ት/ቤት በነበሩበት ወቅት በሃይማኖታቸውና በግብረ ገብነታቸው በጓደኞቻቸው መሐል የታመኑና የተወደዱም ነበሩ፡፡ የተጣሉትን መምከርና በማስታረቅ የወንጌልቃል አንዲስፋፋ በመቀስቀስ ይሳተፉ ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ በት/ቤት በ፲፱፻፴፱ የተጀመረው የካቶሊክ ሚሲኖዊያን የሃይማኖት ቅሰጣን ለመከላከል የተጣሉትን ማስታረቅና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚል ሸፋን የተቋቋመው ማኅበርበአቶ አበበ ከበደ አሰተባባሪነትና መሪነት በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ ቅጽር ግቢ ውሰጥ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ ይኸው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሰንበት ትምህርት ማሰተማሪያ በመሆኑ በየእሁድ ጠዋት በቤተ ከርስቲያኑ ውስጥ በእቅድና በሥነ ሥርዓት የሚከናወን ሰፊ መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጥበትን ማኅበርን እንዲሆን በማስቻል መስርተዋል በኃላፊነትም መርተዋል፡፡

በ፲፱፻፵፱ ዓ/ም “ተምሮ ማስተማር ማኅበር” ተብሎ የተሰየመው ማኅበር አቶ አበበ እውቀታቸውን ገንዘባቸውንና ትርፍ ጊዜአቸውን መስዋዕት አድርገው በማደራጀታቸው እስከዛሬ ድረስ ዓላማውንሳይስትና ሳይፈልስ እንቅስቃሴው ሳይዳከምና ሳይታጎል እያደገ ብዙ ለሆኑ ወጣቶች ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ከመስጠቱ በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች በጀማሪነቱና በዘላቂነቱ ቋሚ አርአያ ለመሆን በቅቷል፡፡

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መኩሪያ የነበሩት አቶ አበበ ከበደ ያበረከቱት አገልግሎት በዚህ ሳያበቃ የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ዘመናዊ አደረጀጀትና አመራር እንዲያገኝ አንዲሁም ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በገዳሙ ሥርም ዘመናዊ ት/ቤት ተመስርቶ አኩሪ ደረጃ ላይ እንዲደርስ መነሻውንና መድረሻውን ቀይሰው እንዲመሠረት በማድረግ የመመጀመሪያ የቦርድ አባልም በመሆን ከፍተኛ ድርሻና አስትዋጽዖ አበርክተዋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ ለቤተክርስትያን ና ለአባቶች ፍጹም ቅን ሰው ነበሩ፡፡አባ ተክለማሪያም ለደጃዝማች ወልደሰማዕት  እንደነገሯቸውና ለዚህ ጥናት አቅራቢ እነደነገሩት የም.ሥ.ኅ.መ ገዳም በገቢ እጥረት በተቸገረ ጊዜ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ ዘንድ ቀርበው ሁሉ አድባራትና ገዳማት መተዳደሪያመሬት ሲኖረው ምስካየ ኅዙናን ብቻ ለምን ሳይኖረው ቀረ መነኮሳቱ ችግር ላይ ናቸው ይረከቡኝ ባሉአቸው ወቅት ንጉሡም ሁሉም ይነጠቃል ይወስድበታል ይልቅ ገዳሙንከአበበ ከበደ ጋር ተማከሩና ራሱን እንዲችል አድርገው ብለው ትንቢት አዘል ንግግር ስለመለሱላቸው ከአበበ ከበደ ጋር ሲማክሩገዳሙ እስከዛሬ አበል የሚያገኝበትን የባንኮ ዲሮማ ህንጻን አክሲዮን እያገኘ እንዲጠቀም የሚያስችለውን መንገድ በመፍጠር ጠቃሚ ስራ አከናውነዋል፡፡በወቅቱ ገዳሙና መነኮሳቱ ከፍተኛ አድናቆትን  ያገኙበትን የስጋጃ ስራን ዕውን እንዲሆን ከሃሳብ ማመንጨት ጀምሮ በተግባር እንዲውል ያደረጉሰው ነበሩ፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ተክለማሪያም በእግራቸው ለሥራ ጉዳይ ሲሄዱ ተመልክተው ወዲያውኑ ገዳሙ እስከዛሬ እየተጠቀመበት የሚገኘውን ቮልስዋገን መኪና ከካምፓኒው እንዲገዛ ያደረጉም ቅን ሰው ነበሩ፡፡

አበበ ከበደ ህይወታቸውን ሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ መንፈሳዊ ስራ ላይ የነበሩ አገራቸውንና ቤተ ክርስትያናቸውን በቅንነት ያገለገሉ ባለ ራዕይና ውዳሴ ከንቱን የሚጠሉ ታላቅ ሰው ነበሩ ፡፡በዚሁ ቅን አገልግሎታቸውና ታታሪነታቸው ከፍ ላለ ኃላፊነት ስለአስመረጣቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት በሥራው ዋና ኃላፊ ሆነው ከየካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ.ም ጀምሮ በብቃት ይወጡት እንደነበር ታውቋል (በሪሁን ከበደ፡ ፲፱፻፺፫፣ መርጌታረታ አሣልፍ)፡፡

ይህድርጅት በ፲፩ ቦርድ አባሎች

(ልዑል አልጋ ወራሽ ልዕልት ተናኜ ወርቅና ፓትሪያርያርኩን ጨምሮ የነበሩበት የነበረ ሲሆን አቶ አበበ ከበደ በኃላ ፊት እንዲመሩት ሲደረግ ሁለት ቦርድ የነበረውን ማለትም አንዱ የዲሬክተሮች ቦርድ ሁለተኛው የበላይ ጠባቂ ቦርድን በአንድ አጠቃለውና የዲሬክተሮች ቦርድ እንዲነሳተደርጐ ሁሉንም አጠቃለው እንዲሠሩት ተደርጓል፡፡ አበበ ከበደም ወደ ድርጅቱ ከመጡ ጀምሮ ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ ነበር (በሪሁን ከበደ ፲፱፻፺፫)፡፡

ይህንንም ከፍተኛ ኃላፊት ከተረከቡ በኋላ በድርጅቱ ሥር ይተዳደሩ የነበሩትን

ሀ/ በደብረ ሊባኖስ በሐረርጌ የሚገኙ የአረጋውያን መጦሪያ ቤቶች በተሻሻለ ሁኔታ እንዲያገለግሉና አንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡

ለ/  እናት አባት የሌላቸው ሕፃናት በልዩ ልዩ እንክብካቤ የሚያድጉባቸው ቤተ ሕፃናት እንዲያስፋፉ ወጣቶቹም በቀለምና በሙያ ትምህርት በተሻለ ሁኔታ እንዲማሩና እዲሰለጥኑ

ሐ/ ረዳትና ወገን የሌላቸው ደካሞች ጤናቸው የሚጠበቅበትና የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች እንዲሻሻሉና እንዲስፋፉ፤

መ/ በተፈጥሮና በልዩ ልዩ እክል ምከንያት ብርሃናቸውን ያጡ  ዓይነ ስውራን በልዩ እንክብካቤ ተይዘው እውቀትና ከፍተኛ ሙያ  የሚገበዩባቸው ትምህርት ቤቶች ዘመናዊና ዘላቂነትባለው መንገድ እንዲደራጅና እንዲስፋፋ በማድረግ እጅግ ብዙ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መገልገያ እንዲሆኑ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በድርጅቱ ሥር ከነበሩት ከሕፃናት ማሳደጊያዎችና ከሰበታ መርሐ ዕውራን* ት/ቤት ጀምረው በልዩ ልዩ ሙያ ሠልጥነው ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን በብቃትና በኩራት ያገለገሉበርካታ ዜጎችን አፍርተዋል፡፡  በአሁኑ ወቀት በስፋት አልግሎት ከሚሰጡት የቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ወ/ሮ በለጥሻቸው ክሊኒክ የአክሱም  ቅ/ማርያም ሆስፒታል ወዘተ ለአብነት ያህልየሚጠቀሱ በአቶ አበበ ከበደ አማካኝነት የተሠሩና የተደራጁ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ናቸው፡፡

*የዚህ ጥናት አቅራቢ ማረጋገጥ ባይችልም መርሐ ዕውር የሚለው ስያሜ ና ቃል በአጋጣሚ ይሁን ወይም በሌላ ከኣጼ ሱስንዮስ ካቶሊከመሆን ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው፡፡ ይኸውም መርሐ ዕውር ትምህርት በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ እራሱን የቻለ የቁጥር ትምህርት (የዘመን አቆጣጠር ስልት) ሲሆን በ፲፯ኛው ምዕት ዓመት ኣጼ ሱስንዮስ የካቶሊክ ዕምነትን ከተቀበሉ በኋላ መርሐ ዕውር መጽሓፍ እንዲጠፋ አዘው ነበር፡፡ዓቃቤ ሰዓት አቦሞ የሚባል ሊቅ መጽሐፉን ይዞ በረሓ በመሄድ እዚያ ትምህርቱን እያሰላሰለ ጊዜው እስኪያልፍ ድረስ ቆይቶ አጼ ፋሲለደስ ሲነግሥ ተመልሶ በመምጣት ትምህርቱን አሰፋፍቶታል፡፡(ስርግው ሀብለሥላሴ የአማርኛ የቤተክርስትያን መዝገበ ቃላት) ፡፡

በአገራችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አካል ጉዳተኞች ብርሃናቸውን ያጡ ዓይነ ሥውራን ደካሞች ወዘተ በዘመናዊ ተቋም ተደራጅተውናተባብረው በአንድነት ሠርተው ሕይወታቸውን መምራትና ከሁሉም ጋር በእኩልነትና እየሰሩ መኖር እንደሚችሉ የታየበትና የተመሰከረበት በሃገራችን የመጀመሪያ ሃሳብ የነበረውን “የተዋህዶ ጥበብ የጃንጥላና የባትሪ ድንጋይ ፋብሪካ” በእሳቸው መሪነት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር፡፡ ይህም በአርአያነቱ የወጭ አገር አጥኚዎችን ሳይቀር የሚስብና የሚጎበኝ ድርጅት ነበር፡፡

እነዚህን በመሳሰሉ በጎ ሥሪዎች በመሳተፋቸውና በመደበኛው ሥራቸውም አኳያ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመታወቃቸው ጄኔቭ የሚገኘው የዓለም አብየተ ከርስቲያናትና ናይሮቢ ኬንያ ላለው የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤዎች ቋሚ የምክር ቤት አባል ሆነው በመመረጥ አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስትያን ኢንተር ቸርችኤይድ ኮሚቴ ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡እያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛና ግብር ከፋይ አንድ ብር በወር በማዋጣት በመንገድ ላይ በልመና ላይ የተሰማሩ ሁሉ አምራች ዜጋ የሚሆኑበት ልመና የሚቀርበትን ኘሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥናት አቅርበው እንደነበረምታውቋል (ታደሰ መንግሥቱ፲፱፻፺፮)፡፡

እኚህ ታላቅ ሰው በቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት ባለአደራዎች የሥሪ አስፈፃሚ መማክርት የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት እንደራሴ በመሆንም አገልግለዋል (በሪሁን ከበደ ፲፱፻፺፫)

አቶ አበበ ከበደ ለፈጸሙት በጎ ሥራዎችና ለአገራቸው ለሰጡት ሰፊ አገልግሎት የዳግማዊ ምኒልክ የመኰንን ደረጃና የኢትየጵያ የክብር ኮከብ የትላቅ መኰንን ኒሻኖች ተሸልመዋል፡፡

አቶ አበበ ከበደ (ገብረ ኪዳን) ከወ/ሮ ጥሩወረቅ አስፋው(ወለተ ማርያም)ጋር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደንብና ሥርዓት ሚያዚያ ፳ ቀን ፲፱፻፶፭ዓ.ም መ ም.ኅ.መ.ገ በተክሊል ተጋብተው ቆርበዋል፡፡ በፍቅርና በሰላም በመተጋገዝ በመረዳዳት መልካምየቤተሰብ መሪነታቸውን ከማስመስከራቸውም በላይ የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡

አቶ አበበ ከበደ ከዚህ ዓለም አልፈዋል፤ስለ ህልፈታቸው ምክንያት ግን ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡መረጌታ ረታ አሳልፍ በሰኔ ፳፪ ቀን ፲፱፻፰፮ ዓ.ም በደርግ መንግሰት ታስረው ባልታወቀ ስፍራ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም እንደተገደሉ ገልጸዋል ፡፡ ይህንኑ ሃሳብ ቀኑን ባይገልጹም ፐሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምም ጽፈውበታል፡፡በደርግ መንግሥት ከተገደሉ ና በተለምዶ ፰ ዎቹ በመባል የሚታወቁት በንጉሡ ጊዜ የነበሩ ከፍተኛ የሀገሪቱባለሥልጣኖች መታሰቢያ መጽሄት ላይ እንደተገለጸው ሐምሌ ፮፣ ፯ ወይንም8 በግፍና በራሥ ካሣ መኖሪያ ቤት በነበረውና በተለምዶ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ግቢ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ መሆኑን ይገልጻል ፡፡

ለሞት የሚያበቃ ምን ክስ እንደነበረባቸው የዚህ ጥናት አቅራቢ  ለማየት ሞክሯል፡፡

አበበ ከበደ በሕይወት እያሉከሚናገሯቸው አንዱ ክርስትና እስከ ሞት ድረስ የሚጸኑበት ነው የሚል ነበር (መምህር ታዬ አብርሓም ፲፱፻፺፮)፡፡እኚህ በሕይወቴ ከያዝኩት እንደ በጎ አድራጎት ስራ ስክትክት የሚልልኝ የለም ብለው የሚያምኑት ቅን ሰው በደርጎች እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ መገመት አያቅትም (ታደሰ መንግሥቱ ፲፱፻፺፮) ፡፡

የዚህ ጥናት አቅራቢ የተከሰሱበትን ለማወቅ ጥረት ሲያደርግ ያገኘውም መረጃ ሶስት ዓይነት ሆኗል ፡፡

ምስክርነት በባለ ሥልጣናቱ አንደበት በሚል ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ ግንቦት ፳፻፩ ባሳተሙት መጽሓፍ እንደገለጹት  የስድሳዎቹ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አሟሟት ውሳኔ አሰጣጥን አስመልክቶ በጊዜው በስብሳባ ለይ ተገኝተው ምርመራውን ያደረጉ ሰዎች (መንግሥቱ ገመቹ ወይንም በሻምበል ገብረየስ ወልደሃና እንደጻፉት የሚገመት) የደርግና የንዑስ ደርግ አባላት አሠራርን ያሳየ የልዩ ዐቃቢ ሕግ ፅሕፈት ቤት  ክስ ላይ ባቀረበው ሰነድ ፺፣፻ ከተሰኘው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተራ ቁጥር ፳፫ ላይ የአበበ ከበደ ስም ተፅፎ የተሰጠው ምክንያትወይም ለሞት ያበቃቸው “አስቸጋሪ ነው” የሚል ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ በከንቱ ያለ ኃጢያታቸው ከግፈኞች ዕጅ መስዋዕትነትን ሊቀበሉየቻሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ሁለተኛው የቅርብ ጓደኛቸው የሆኑት ቀሲስ ታደሰ መንግሥቱ እንደሚገምቱትና እንደሚባለው ብለው እንደተናገሩት የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥትን ደርግ በሀሰት ከከሰሳቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ ፲፫ ቢሊዩን ዶላር በውጭ አገር ደብቀው አስቀምጠዋል የሚል ሲሆን አበበ ከበደም ለንጉሡ ቅርብ ስለነበሩ ና ለዓለም አብያተ ክርስትያናት ኅብረት ጽ/ቤት አገልግሎት እንዲሁም ለሚመሩት የቀ.ኃ.ሥ በጎ አድራጎት ድርጅትና ሌሎች ስራዎች ወደ ጄኔቭ ይመላለሱ ስለነበር የሚያውቁት ይኖራል በሚል ወይንም ገንዘብ በማሸሽ ተባብረዋል በሚልየሐሰት ክስ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል፡፡( ታደሰ መንግሥቱ ፣፲፱፻፺፮)

ይሁንና ይህንን ጉዳይ ማረጋገጥ ደርግ ራሱም አልቻለም ከዚሁ ክስ ጋር በንጉሡ ላይ ቀርቦ የነበረው ሌላው ምከንያት ወርቅ ደብቀዋል የሚል ሲሆን በጅሮንድ ገዛኸኝ ገብረ ማርያም ላይ ምርመራም ተደርጐ ነበር፡፡ ይህም ከአበበ ከበደ ጋር አብረው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የመጀመሪያው በቦርድ ውስጥ ይሠሩ የነበሩት በጅሮንድ ገዛኸኝ ገብረ ማረያም በሰጡት ቃልና ደርግም ኅዳር ፫ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም በአወጣው መግለጫ አንድም ወርቅ የጠፋ ወይንም የተሰወረ ነገር እንዳልነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ (በሪሁን ከበደ፤፲፱፻፺፫)፡፡

ሶስተኛው የትምህርት ቤት ጓደኛቸው ዶ/ር አክሊሉ ኃብቴ በቀጥታም ሳይሆን ከሰዎች እንደሰማሁት ብለው ለዚህ ጥናት  እንደገለጹት በንጉሠ ነገሥቱ በኩል ታማኝ ስለነበሩና ስራቸውንም በትጋት የሚሰሩ በመሆኑእርሳቸውም ፖለቲካውን እንዲቀበሉይፈልጉ የነበሩና ጥያቄውን ያልተቀበላቸው  ለአገሪቷ የሚጠቅማት ኮሚኒዝም ነው የሚሉ የግራ ፖለቲካ አራማጆች በጥላቻ ና በቂም በቀልገድለዋቸዋል ወይንም አስገድለዋቸዋልየሚል ነበር ፡፡አበበ ከበደ የእምነት ፀር የሆነውን ኮሚኒስትነትንይጠሉም እንደነበር ታውቋል፡፡

የሆነ ሆኖ እግዚአብሔር እንደፈቀደ እኚያ የተምሮ ማሰተማር አዳም እኚያ የሰንበት ትምህርትቤቶችመሥራች እኚያ ባለራዕይእኚያ  የነዳያን ረዳት ና ተስፋቸው የነበሩ ታላቅ ሠውሕይወታቸውበአሰቃቂ ሁኔታ በግፈኞች እጅ አልፏል፡፡

ለሀገርና ለወገን መገልገያ እንዲሆኑ ያነጹዋቸው ተቋሞች ግን ዘለዓለም ይኖራሉ፡፡ አቶ አበበ ከበደ እንደ አንድ ሻማ ሆነው በርተውና ተቃጥለው ጨለማውን ያስወገዱላቸው ማኅበራትም ለሌሎች የሚያበሩ የብርሃን ምንጮች ሆነዋል፡፡ በመልካም ሥራዎቻቸው ለዘለዓለም ሲታወሱ ሲመሰገኑና ሲከበሩ ይኖራሉ፡፡ይላል የሕይወት ታሪካቸው የተፃፈው መፅሔት፡፡

“…. መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤

ሩጫዬንም ፈጽሜያለሁ ሃይማኖቴንም

ጠብቄያለሁ እንግዲህስ እውነተኛ

ፈራጅ የሆነው ጌታ ያዘጋጀልኝን የጽድቅ

አክሊል ይሰጠኛል”

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro