ከሶስቱ አባቶች ፪ ታደሠ መንግሥቱ

የተምሮ ማሰተማር መቅረዝ “የፍቅር የትህትናና የጽናት አባት” ( ሥመ ክርስትና ንዋየ ማርያም)፡፡

ቀሲስ ታደሠ መንግስቱ የተምሮ ማስተማር ማህበር መቅረዝ፡፡ (ፎቶ ከተምሮ ማሰተማር ማኅበር)

ከአዲስ አበባ ሦሰት ኪሎ ሜትር እርቆ በሚገኘው እንጦጦ ማርያም አካባቢ በ ፲፱፻፲፰ ዓ.ም መጋቢት ፳፫ ቀን ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው መምህር መንግሥቱ ወ/ሚካኤል ይባላሉ፡፡ የእናታቸውም ስም ወ/ሮ አፀደ ነው፡፡ በስድሰት ዓመታቸው እናታቸው በአሥር ዓመታቸው ደግሞ አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን አሥራ ስድሰት ዓመት እስኪ ሆናቸው ድረስ እዛው እንጦጦ ኖሩ፡፡ በእንጦጦ እያሉም ውዳሴ ማርያም ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡ ከአቡነ አብርሃም እጅ ማዕረገ ዲቁናም በመቀበል በእንጦጦ ማርያም ቤ/ክ አልግለዋል፡፡ ቅኔ ለመማር ዝግጅት ላይ አያሉ አጎታቸው ወደ አዲስአበባ ይዘዋቸው ስለመጡ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት ለመከታተል ተገደዱ፡፡ እዚህም አዳሪ ት/ቤት እስኪ ገቡ ድረስ በመንበረ ልዑል ቅ/ማርቆስ ቤ/ክ ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ን.ነ ቀ.ኃ.ሥ በሚያስቀድሱበትም ወቀት በድምጻቸው መልካምነት እየተመረጡ ይቀድሱ ነበር፡፡

በዘመናዊ ትምህርት በጣም ዕድለኛ ነኝ የሚሉት ታደሰ መንግሥቱ በትምህርት ብዙ እንዳልተቸገሩ ከ፩ኛ እስከ ፲፪ኛ ክፍል ድረስ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት እንደተማሩ ጊዜውም ከ09)#5 እስከ ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ለዘጠኝ ዓመታት እንደሆነ በወቅቱ ፲፪ኛ ክፍል ላይ የማትሪክ ፈተና ከእንግሊዘ እየመጣ እንዲፈተኑ ይደረግ ነበር በማለት ገልፀዋል፡፡ ያኔ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ ወደ ውጭ ሄዳችሁ ትማራላችሁ ተብለው በጣም ጉጉቱ አደሮባቸውም ነበር፡፡ ከሚወስዱት ሰባት ፈተናዎች ወስጥ አንድ እንኳን የወደቀ እንዲደግም ይደረግ ነበር (ሪፈር ይሉታል)፡፡ ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ተማሪዎች በመውደቃቸው ምክንያት ተማሪዎች ሲያልፉ አንድ ላይ ነው የምትሄዱት ጠብቁተብለው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡

በመጨረሻ ደግሞ ዩኒሸርሲቲ ኮሌጅ ስለተከፈተ መጀመሪያ ሁለት ዓመት እዚህ ተምራችሁ ትሄዳላችሁ በመባላቸው ትምህርት ጀምረዋል፡፡ እርሳቸውም ከሌሎቹ ከፍያሉ (ትልቅ) ስለ ነበሩና እድሜአቸውም እየጨመረ ስለሄደ፣ሥራ ፈልገውገቡ፡፡ በስራ ላይ እያሉም በማታው መርሐ ግብር የሕግ ትምህርት ቀጥለው የነበረ ቢሆንም ሦሰት ዓመት ከተማሩ በኋላ ጤናቸው በመታወኩ መቀጠል አልቻሉም፡፡ በሌላ ጊዜም ሳይኮሎጂ ና ሶስዮሎጂ ትምህርት ጀምረው ስላልተመቸቻው ብዙም አልገፉበትም፡፡

በሥራም የሠሩበት መስሪያ ቤት በአንድ መሥሪያ ቤት ብቻነው፡፡ እሱም የግ.ቀ.ኃ. ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ጽ/ቤት እና የጸሕፈት ሚኒስቴር የሚባሉ መስሪያ ቤቶች (በአንድ ላይ የሚሠሩና አንድ ናቸው) ውስጥ በተርጓሚነት አገልግለዋል፡፡ በደርግ መንግሥት መሥሪያ ቤቱ ተዘግቶ በምትኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሲባል ለሰባት ዓመታት ሰርተዋል፡፡

ሥራ ሲጀምሩ ተርጓሚ ተብለው ገቡ ከዛም የክፍል ዳሬክተር ዋና ዳሬክተር በ ፲፱፻፶፬ ዓ.ም ገደማ ረዳት ሚኒስቴር ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በ፲፱፻፸፫ ዓ.ም መጋቢት ፳፫ ቀን ልክ በ፶፭ ዓመታቸው ጡረታ ወጥተዋል ፡፡

የተምሮ ማሰተማር ማኅበርን ከመሠረቱት አባላት አንዱ የሆኑት ታደሠ መንግስቱ በ፲፱፻፴፱ዓ.ም የተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ሳሉ የተጣሉትን ለማስታረቅ በሚል በኅቡዕ በተመሠረተው ማኅበር መስራች በመሆን ይሰባሰቡ እንደ ነበር ተናግረዋል፡፡ በዚያ ስብስብ ውስጥ ቀስ በቀስ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ይማማሩም ነበር፡፡ ይህም እያደገ ሄዶ በም/ኅ/መ/ገ እሑድ እሑድ በሦሰት ሰዓት ቤተክርስቲያኑ ተከፍቶላቸው ከእቴጌ መነን ተማሪዎች ጋር በመቀላቀል በአቡነ ናትናኤልና በአቶ አበበ ከበደ ከፍተኛ ጥረት በገብረ ጊዮርጊስ አጋዤ ስያሜ አውጪነት የተምሮ ማሰተማር ማኅበርን መተዳደሪያ ደንብ ተሰርቶለት በ፲፱፻፵፱ዓ.ም መሥርተዋል፡፡ አገልግሎቱን አስፍተዋል፡፡ አባልና መስራች የሆኑት በዚህ መልኩና ከዚያን ጊዜ ማለትም ከ፲፱፻፴፱ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ ቀሲሥ ታደሰ መንግሥቱ ከም.ኅ.መ. ገዳም ጋር የተዛመዱት ገና በልጅነታቸው ሲሆን፣ አሁን ያለው የገዳሙ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሲገነባ ምርጥ ምርጡን የመዓዘን ድንጋይ በማቀበል የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ሆነው እርሳቸውም ራሳቸው እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ የከበረ የተመረጠ የተወደደ ማዕዘን ሆነው ዘልቀዋል፡፡

ቀደም ባለው ዘመን በ፲፱፻፴፱ ና ፲፱፻፵ዎቹ በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ከመሰል የት/ቤቱ ባልደረቦቻቸው ጋር (የዛንጊዜዎቹ እነ አቶ አበበ ከበደ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት አቶሥዩም ወ/አብ አቶ መኮንን ዋሴና ሌሎችም ጋር በመሆን በት/ቤቱ ውስጥ ያጋጠማቸውን በኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታቸውና እምነታቸው ላይ ያንዣብብ የነበረውን ክስተት በመቋቋም ያከሸፉበት የኅብረት ክንዋኔ አቸው ጀምሮ ለሃይማኖታቸው በጽኑ ቆራጥነት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚያን ወቅት ለነበረው እንቅስቃሴአቸው መሪ አርበኛው አቶ አበበ ከበደ እንደነበሩ ቀሲስ ታደሰ አረጋግጠዋል፡፡

ታደሠ መንግሥቱ ትሑትና ለመንፈሳዊ ስራ እልኸኛ ወስጡ እውነትን የተሞላ ግንደ ግሞ ሆደ ባሻና እንባ የሚቀናው ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ የሚጠላ ሰው ነበር ይላሉ የትምህርት ቤት ጓደኛቸው ደጃዝማች ወልደሰማዕትገብረወልድ፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ፈርቀዳጅ የሆነውን የተምሮ ማስተማር ማኅበር ከጥንስሱ ጀምሮ ከአቶ አበበ ከበደና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን መስርተዋል፡፡ በደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ገብረ ወልድ አሳሳቢነት በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የነበረውን የጄስዊት ኢየሱሳውያን ካቶሊኮችን የቅሰጣ ስራ ተቃውመዋል፡፡ በመሩትም ተቃውሞ እንዲከሽፍ አድርገዋል፡፡ ከአቶ ገብረ ጊዮርጊስ አጋዤና ከሌሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ ውስጥ መሠረት በመጣል እጅግ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ታደሰ መንግሥቱ የተምሮ ማስተማር ማኅበርን ከመመስረት አልፎ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ ከአባልነት እስከ ማኅበሩ የበላይ ኃላፊነት ባሉት የሥራ ድርሻዎች እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዚሁ ማኅበር ውስጥ ለተከታይ ትውልድና ለምዕመናን ጭምር አስተማሪና አርአያ በመሆን በየበዓላቱ ዛሬ መዘምራን የሚለብሱትን የማኅበሩ መለያ በመልበስ በመዘመር እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል ፡፡ ታደሠ መንግሥቱ ማኅበሩ የጥምቀት በዓልን በጃንሜዳ ሲያከብር በዐውደ ምህረት በማስተማር በመዘመር በወቅቱ የተማረ ና ባለስልጣን ሆኖ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት እንደኋላ ቀር በሚቆጠርበት ዘመን አርአያ ሆነዋል፡፡ በተምሮ ማሰተማር“ ሰንበት ትምህርት” ቤት ከሰጡት ድካም ያልተለየው አገልግሎት በተጨማሪ የትህትና አስተማሪና አባት በመሆን የፈጣሪያቸውን ፈለግ ተከትለው ክርስትናን በቃል ሳይሆን በመኖር በሕይወታቸው ያስተማሩ አባት እንደሆኑ የተምሮ ማስተማር ማኅበር የረዥም ዘመናት ቋሚ ምስክራቸው ነው፡፡ ታደሠ መንግሥቱ ተምሮ ማስተማርን እንደ መቅረዝ ሆነው ብዙዎች ወጣቶችና ምዕመናን ብርሃናቸው እንዲበራ አድርገዋል፡፡ በህይወታቸው ሳሉ መመስገንን የማይፈልጉ ነበሩ፡፡

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro