ከሶስቱ አባቶች ፩ አባ ሐና ጅማ

እንደ አቶ አርአያ ተገኝ ገለፃ አባ ሐናጅማ የተወለዱት ሚዳ ወረሞ በሚባል ስፍራ ነው፡፡ ትክክለኛ ስማቸውም አባ ገብረ ሐና ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ለማሳጠር አባ ሐና እያለ እንደሚጠራቸው የቤተክርስትያን መረጃዎች በሚል በዲ.ዳንዔል ክብረት የተፃፈው መፅሐፍ ይገልፃል፡፡ከበደ ተሰማ የታሪክ ማስታወሻ በሚለው መጽሃፋቸው ሺበሺ ጅማ በሚል መጀመሪያ ላይ ተጠቅመው በቅንፍ አባ ሐና ጂማ ብለው ጽፈዋል ፡፡ በሊቅነታቸውና በቀልዳቸው ከሚታወቁት አለቃ ገብረሐና ለመለየትም ሲባል ይሆናል አባ ሐና በሚባል አጭሩ ስማቸው የተጠሩት፡፡

አባ ሐና ጅማ ምንኩስናን የተቀበሉት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ነው በዚሁ ገዳምም በረድዕነት አገልግለዋል፡፡

ዐፄ ኃይለሥላሴ ሥልጣን እንደያዙ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአባቶች ቤተክርስትያን ለማሠራትና ለሀገራችንም ለቤተክርስቲያናችንም በአግባቡ እንዲውል የሚረዳን ያስፈልገናልናሰው ስጡን ብለውገዳሙን ቢጠይቁ ይህን ሥራ ከአባ ሐና በቀር ማንም አይሰራውም ተብለው የግምጃ ቤቱ ኃላፊ እንዳደረጓቸው ዲያቆን ዳንዔል ክብረት ገልጠዋል፡፡

በመንፈሳዊነታቸውና በትጋታቸው የሚታወቁት አባ ሐና ጠንካራ ሰራተኛችን በፍቅር ማሰራትን እንጂ በበላይነት ማዘዝን የማይወዱ እንደነበሩ አቶ አርአያ ለዲያቆን ዳንዔል እንደ ነገሩዋቸው በጥናታቸው ላይ ጽፈዋል፡፡

አባ ሐና የተምሮ ማስተማር ማኅበር እንዲጀመር አባላቱ እንዲበዙና ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምሮ መኳንንቱና መሳፍንቱ አባል እንዲሆኑ በሀብት እንዲበለጽግ ታላቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡(ዲ.ዳንጌል ክብረት ፲፱፻፺፱).

አባ ሐና በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በግርማሜ ንዋይ እጅ በጥይት ረቡዕ ለኀሙስ ሌሊት ታህሳስ ፫ ቀን፣ ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ተገድለዋል እሁድ ዕለትም በደብረ ሊባኖስ እንደ አቶ አርአያ ግምት በ፸ ዓመታቸው ተቀብረዋል፡፡ (ዲ.ዳንኤል ክብረት ፲፱፻፺፱).

አባ ሓና ጂማ ከታቦተ መድኃኔዓለም ና ከም.ኅ.መ.ገ ጋር የተለየ ታሪክ ያላቸው ገዳሙን የመጀመሪያ የበላይ ጠባቂ ሆነው ያሰተዳደሩ በስደት በእንግሊዝ ሃገር መንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡ በተለይም የተፈሪ መኮንን ተማሪዎችን የመንፈስ አባት በመሆን ያገለገሉ አባት ነበሩ፡፡

የተምሮ ማስተማር ማኅበር መታሰቢያቸውን ሚያዚያ ፳፯፣፲፱፻፶፫ ዓ.ም ሲያደርግላቸው የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል (መዝ.፩፻፲፩) በሚል ርዕስ ባሳተመው ጽሑፍ የሕይወት ታሪካቸውንና የሰሩትን መልካም ፍሬዎችን ከዘረዘረበኋላ “እስከ መጨረሻው የታመንክ ሁን “ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን በመፈጸም ከጉድለትና ጥፋት ርቀው ቅን አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ በታህሣሥ ፯ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም የሞት ግዳጃቸውን በግፍ እንደ ተቀበሉና በገዳሙ ውስጥ ለተቋቋመው የተምሮ ማስተማር ማኅበር ሥራው የሚደረጅበትን እርምጃው የሚፋጠንበትን የሃብትና የጉልበት እንዲሁም የምክር እርዳታቸውን ያለማቁዋረጥ ያበረከቱለት እንደነበር፡፡ በመግለጽ እኒህን ታላቅ አባት በማጣቱ ማኅበሩንየሚሰማው ኀዘን እጅግ የመረረ ሆኖ ይገኛል በማለት ኀዘኑን በጽሑፍ አሥፍሮታል፡፡

አባ ሃና ጅማ (ፎቶ ከተምሮ ማስተማር ማኅበር)

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ታህሳስ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ባወጣው ጽሑፍ “በፖለቲካ ወይም በሥልጣን የአስተዳዳር ኃይል የሌላቸውን አባ ሐና ጂማን ገድለዋቸዋል፡፡ እኝህ ለወገኖቻቸው መንፈሳዊ ዕድገት የሚጥሩት የእግዚአብሔር ሰው በጾምና በጸሎት ዕድሜያቸውን ሙሉ የደከሙ ነበርሲል በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ የተፈጸሙባቸውን ግድያ ገልጧል፡፡

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro