የሐዋርያት ጾም እና የሐዋርያት ሰማዕትነት

በመምህር ሲሳይ አበበ

“የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጾመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጾሙት ስለ ምንድን ነው? አሉት:: ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ:: በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል::” (ማቴ 9:14-17)

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ራሱን በሙሽራ፤ ደቀ መዛሙርቱን በሚዜ መስሎ፣ ጾም መጾም ያለበት በሐዘን በለቅሶ እንደሆነ አስቀድሞ በተናገረበት ወቅት “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” (ኢዩ 2፡12) እንዳለው፤ ነቢዩ ዳንኤልም “በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ፡፡ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም” (ዳን 10፡2-3) በማለት የጾም ወቅት የሐዘን ጊዜ መሆኑን ጠቁሟልና፡፡

አምላካችንም የእኔ ደቀ መዛሙርት እኔ ከእነርሱ ጋር ሳለሁ በጾም ማዘን አይቻላቸውም አለ፡፡ ነገር ግን ወደፊት መጾም አይገባቸውም አላለም፡፡ እኔ ከእነርሱ የምለይበት ጊዜ ይደርሳል ያንጊዜ ይጾማሉ አላቸው፡፡ ይህ ጊዜ መቼ ነው? የሚለውን ጥያቄ የተመለሰው በጌታ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም ወቅት “ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል”፡፡ የሚወሰደው በሁለት ወገን ነው፡፡ አንደኛ በመስቀል ሞት፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሞት ተነሥቶ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ወቅት ሲሆን፣ በእነዚህ በሁለቱ ወቅት ሐዋርያት ጾመዋል፡፡

በአንደኛው በሞተበትና በመቃብር በቆየበት ወቅት አምላካችን ተቀብሮ ከሙታን ሳይነሣ አንበላም ብለው ሁለት ቀን ጾመው አክፍለዋል፡፡ የእነርሱን አብነት አድርገን እኛም ክርስቲያኖች የክርስቶስን በመቃብር መቆየት ለማሰብ ሁለት ቀን ባለመብላት እናከፍላለን፡፡ በሁለተኛው በምወሰድበት ያለበት ደግሞ ወደ ሰማይ ሲያርግ በመንፈስ ቅዱስ ታድሰው የጾሙት ጾም ነው፡፡

ያረጀ ልብስ ላይ፣ አዲስ ቁራጭ ጨርቅ ቢሰፋበት፣ በመጠኑ የተቦጫጨቀውን ልብስ ቀዳዳ እንደሚያባብሰው፤ እንደዚሁም በፍርሐት ያሉት ሐዋርያት፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ካልተጽናኑና ካልታደሱ ጹሙ ቢሉአቸው አይችሉትምና፤ “መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ” መጥቶ እንዲያጸናቸውና፣ እንዲያጽናናቸው ያስፈልግ ነበር (ዮሐ 14፡26)፡፡ ስለዚህም “እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” (ሉቃ 24፡49) ተብለው ኃይል በሆነው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ታድሰው፣ እሁድ ጰራቅሊጦስ በወረደ በማግስቱ ሰኞ ዕለት ሐዋርያት በዚያን ጊዜ ጾሙ፡፡ ይህ ጾም በሚውልበት ወር ሲጠራ “የሰኔ ጾም”፣ በጾሙት ደቀ መዛሙርቱ ስም ሲጠራ “የሐዋርያት ጾም” ይባላል፡፡ ይህን ጾማችንን በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝተን ከዓመት እስከ ዓመት በመጾም ሐዋርያት ያገኙትን በረከት እያገኘን እንቀጥላለን፡፡

የጾሙ ማጠናቀቂያ ዕለት ሐምሌ አምስት ቀን በጾም እና በጸሎት ወንጌልን በምድር እየዞሩ ሲያስተምሩ ከነበሩ ሐዋርያት መካከል የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ ዕረፍታቸው መታሰቢያ ይደረጋል፡፡

ሊቀ ሐዋርያት የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር ዓሣ በማጥመድ ላይ ሳለ ለሐዋርያነት የተጠራ ሲሆን፤ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በዕድሜ ትልቁ እርሱ እንደነበር ታሪኩ ያሥረዳል፡፡ በባሕር ላይ አግኝቶ ጌታ ሲጠራው ሃምሣ ሦስት ዓመቱ ሲሆን የነበረውን መረብ፣ ታንኳ እና አባቱን ትቶ ጌታን ተከተለ፡፡
ሊቀ ሐዋርያነቱን ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና በጐቼን አሰማራ ተብሎ በወንጌል ቃል እየመገበ ሲጠብቅ ከኖረ በኋላ፣ አምላካችን እንዴት አድርጎ እንደሚሞት አስቀድሞ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው፡፡ በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ” (ዮሐ 2118-19)፡፡

በዓለ ሃምሳ ሆኖ በንጋታው ከጀመሩት የሐዋርያት ጾም ጀምሮ በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ምድርን ዞሮ በወንጌል ካረሳት በኋላ በስድሳ አራት ዓ.ም. የነገሠው ኔሮን ራሱ የሮማን ከተማ በእሳት አቃጥሎ በክርስቲያኖች ስላመካኘ፤ በዚህ ወቅት በእሥር ቤት ታሥሮ የነበረውን ቅዱስ ጳውሎስን በሰይፍ እንዲከለል አደረገው፡፡

በሰይፍ የተከለለው ቅዱስ ጳውሎስ በየዕብራይስጥ ስሙ ሳውል ይባል ነበር:፡ ጳውሎስ ማለት “ንዋየ ኅሩይ /ምርጥ ዕቃ/” ማለት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳንን ትምህርት ከገማልያል የተማረ ሲሆን፤ ብሉይ ኪዳን ያጠፋሉ ብሎ ያሰባቸውን ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ፍቃድ ተቀብሎ እየሄደ ሳለ “…ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን የጌታ ተግሣጽ ሲቀበል፤ ዐይኑ ታወረ፣ ምግብ ሳይበላ ሦስት ቀን ከቆየ በኋላ ሐናንያ ከተባለው አባት ዘንድ እንዲማር እና እንዲጠመቅ፣ ዐይኖ ተፈወሶም ወደ አገልግሎት እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ለሐዋርያት “ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው” ብሎ ባስረዳቸው መሠረት ዓለምን ዞሮ ካስተማረ በኋላ ከላይ እንዳልነው በሮም በነገሠው በኔሮን ተንኮል ምክንያት አንገቱን ተሰይፎ በስድሳ ሰባት ዓ.ም ሐምሌ አምስት ቀን ሰማዕትነቱን ፈጽሟል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ መሰየፍን የሰሙ ክርስቲያኖች “ባይሆን አንተ ትረፍልን” ብለው ቅዱስ ጴጥሮስን በከተማዋ ግንብ በገመድ አሥረው በቅርጫት አውርደው እንዲያመልጥ አደረጉት፡፡ እርሱም ራሱን ሰውሮ በጎዳና ሲሄድ፤ አንድ ቀይ ጐልማሳ መስቀል ተሸክሞ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ፡፡ እየቀረበ ሲመጣ ግን ጌታችን መሆኑን ተረዳ፡፡ ወዲያው በፊቱ ተደፋና፡- “ጌታዬ ወዴት እየተጓዝክ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ጌታችንም “ልሰቀል ወደ ሮም ከተማ እሄዳለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “ዳግመኛ ትሰቀላለህን?” አለው፡፡ አስቀድሞ በምን ዓይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው የነገረውን አስታውሶት እጅግ አዝኖ ወደ ሮም ከተማ ተመልሶ ሲፈልጉት ለነበሩ የኔሮን ወታደሮች “እነሆኝ ስቀሉኝ” ብሎ እጁን ሰጣቸው፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላም ሮማውያን የመስቀያውን እንጨት ሲያቀርቡ ተመልክቶ “እኔ እንደ ጌታዬ ሳይሆን ቁልቁል ዘቅዝቃችሁ ሰቀሉኝ” ብሎ ለመናቸው፡፡ እነርሱም ፈቃዱን ፈጽመውለት ሐምሌ አምስት ቀን በስድሳ ሰባት ዓ.ም ዘቅዝቀው ሰቅለውታል፡፡

የብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ረድኤት በረከታቸው፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ የጸሎታቸው ጸጋ በሁላችን ላይ ይደርብን በጸሎታቸውም ይማረን! አሜን!

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro