“ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር”

(የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማለላሉ።)
መዝ ፵፬፥፲፪
ግንቦት ፳፩ በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መልአክትን አስከትላ ትገለጽላቸው ነበር፤እስላምም ክርስቲያንም በግልጽ ይመለከቷት ነበር። ከየአገሩ ያሉ ሰዎችይሰበሰባሉ ድንኳን ተክለው ሰቀላ ሰርተው አጎበር ጥለው ይከትማሉ ፤ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሳታቋርጥ ትገለጽላቸው ነበር፤ እንዲል ተዓምረ ማርያም !! እንኳን ለእመቤታችን ለወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓሏ በሰላም በጤና አደረሰን አደረሳችሁ አሜን።ከ ፴፫ቱ የእመቤታችን በዓላቶች አንዱ ነው። ደብረ ምጥማቅ በምኔተ ገምኑዲ አቅራቢያ ግብጽ ውስጥ የምትገኝ ቦታ ናት። እመቤታችን በስደት ሳለች ጌታ በዚህ ቦታ በስምሽ ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል ስሙንም ደብረ ምጥማቅ ይሉታል ብሎ ነግሯት ነበር። ይኸውም አልቀረም በዚህ ቦታ በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን ታንጾ ስሙ ደብረ ምጥማቅ ተብሏል። በዚህ ዕለት እመቤታችን ከፀሐይ ፯ እጅ አብርታ ከጉልላቱ ላይ በመንበረ ብርሃን ተቀምጣ መላእክት ሊቃነ መላእክት ከበው ሲያመሰግኗት ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት እጅ ሲነሷት ታይታለች። እስከ ፭ (አምስት) ቀንም ምዕመናኑን አረማውያንም በየ ዓመቱ በእነዚህ ፭ (5) ዕለታት በደብረ ምጥማቅ ተሰብስበው የሚያከብሩት ሆነዋል። እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአውሬው ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረውን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን እመቤታችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሽን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጅሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ “ማርያም ሆይ ስለዚህ ነገር እንወድሻለን እናገንሻለን” ይህንን ቃል የተናገረው አባ ሕርያቆስ ሲሆን ተጽፎ የምናገኘው በቅዳሴ ማርያም ውስጥ ነው፡፡ አባቶቻችን የእግዚአብሔር መንፈስ ስላደረባቸውና የእመቤታችንን ክብር ስለተረዱ እመቤታችንን ያመሰግኗት ነበር፡፡ ሊቁ ስለዚህ ነገር እናከብርሻለን እናገንሻለን ካለ በኋላ “እስመ ወለድኪ ለነ መብልዓ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን” “እውነተኛ የሕይወት መብልንና የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና” አለ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች በኋላም ለአዳም የሰጠው የተስፋ ቃል ሲደርስ እውነተኛ የሕይወት መብልና የሕይወት መጠጥ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውለድ በቅታ የተገኘች እውነተኛ እናታችን ናት፡፡ በእውኑ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረ ማን ነው? እሷንስ ያላወደሰ ማን ነው? በእውነተኛ ህሊና ሆነን ካሰብነው ሌሎች መናፍቃን እንደሚሉት ድንግል ማርያምን ለማመስገን እና ለማወደስ እንዲሁም ለድንግል ማርያም የጸጋ (የአክብሮት) ስግደት ለመስገድ የግድ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አያስፈልግም:: ሰው ሁኖ መፈጠር ብቻ በቂ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ በእናቱ ማኅጸን እያለ ቅድስት፣ ክብርት፣ ልዩ ለምትሆን ለድንግል ማርያም የሰገደው መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ፈልጎ ስላገኘ እንዳልሆነ ሁላችን የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ እርሱ የሰገደላት እውነተኛ ሰው ሁኖ በመፈጠሩ ብቻ ለድንግል ማርያም የተሰጣትን አምላክን የመውለድ ልዩ ስጦታ(ጸጋ) ስላወቀ ነው፡፡ አባቶቻችን ስለ ድኅነት ሲያስተምሩ፣ ሲጽፉ እና በምሳሌም ሲናገሩ ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥም ያለ ድንግል ማርያም የኖሩበት ጊዜ የለም ነበር ወደፊትም አይኖርም፡፡ እዚህ ላይ ነቢየ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የተናገረውን ነገር እናንሳ (መዝሙር 44፡14 ጀምሮ ያለውን) ‹‹ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኩሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር›› ‹‹ገጸ ምሕረትሽን፣ ገጸ ረድኤትሽን ለማግኘት፤ አንድም በቁሙ (በቀጥታ በጥሬ ትርጉሙ) በዚህ ዓለም የከበሩ የገነኑ ህዝቦች ሁሉ ፊትሽን ለማየት ይለምናሉ፡፡ እዚህ ላይ የምንረዳው ነገር የእመቤታችን የድንግል ማርያም ክብሯ አፍአዊ፣ ምድራዊና ስጋዊ ሳይሆን ውሳጣዊ፣ ሰማያዊ እና መንፈሳዊ ነው፡፡ይህም ማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ስጋ፣ ንጽሐ ነፍስ እና ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ የያዘች ልዩ ፍጥረት ስለሆነች ቅዱሳን አባቶቻችን ገጸ ረድኤቷን ለማግኘት ሁሉ ጊዜ በትጋት ይለምናሉ፡፡ አንድ አባ ይስሐቅ የሚባል ቅዱስ ‹‹አርእየኒ እመከ›› ‹‹እናትህን አሳየኝ›› እያለ ሰባት ዓመት ሲጸልይ ኖሯል፡፡ ከዚያም በኋላ እመቤታችን ተገልጻ እረፍትህ ደርሷል፡፡ ክፍልህ ከእኔ ነው ብላው አርጋለች፡፡(ተአምረ ማርያም) ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ቅዱሳን አባቶቻችን እመቤታችንን ያመሰግኑ የነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ አላነብ ብለው ነው? አይደለም፡፡ እነሱማ ከማንበብም አልፈው በሕይዎትም ተርጉመው እየኖሩበት ነው፡፡ መቸም ሁላችንም እንደምናውቀው መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ይልቅመጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ በሕይዎት መኖር ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ስጋዌው ሲያስተምር “ይህንን ቃል አንብቦ፣ ተምሮ እና አስተምሮ ነገር ግን ወደ ተግባር(ወደ ሕይዎቱ የማያስገባው)፣ ወደ ስራ የማይለውጠው ሰው ፊቱን በመስታዎት የሚያይ ሰውን ይመስላል” ብሎ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ አባቶቻችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የማመስገናቸው ታላቁ ምስጢር መጽሐፍ ቅዱስ አላነብ ብለው ሳይሆን ከአምላክ የተሰጣትን ልዩ የሆነ ክብሯን አምላክ በገለጸላቸው መጠን መረዳት መቻላቸው ነው፡፡ ስለዚህ እኛም በዚህ ዘመን ያለን ትውልዶች ሁሉ በቅድስናም ሆነ በእውቀት ከአባቶቻችን አንበልጥምና እውነተኛ የሕይወት መብልና መጠጥ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት ማደሪያ ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ድንግል ማርያምን ማክበርና ማመስገን ይገባል፡፡ አምላካችን ድንግል ማርያምን የምናመሰግንበት መልካሙን አንደበት ክብሯን የምናይበት ውሳጣዊ ዓይነ ኅሊና ያድለን፡፡
አሜን፡፡

ዲ/ን ብዙዓለም አበጀ

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro