ማውጫ

ከቅዱሳን

ድሜጥሮስ ሕጋዊና ድንግል

አዘጋጅ ጉልላት ዮሀንስ

‹‹ መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው ስጦታው ግን ልዩ ልዩ ነው›› የሚለው ቃል እውነት መሆኑን እንረዳለን ታሪካቸው ከሚያስደንቀው ቅዱሳን መካከል በያመቱ በዘመን መለወጫ የሚታወሰውንና የቤተክርስቲያንን የዘመን የአፃዎማትንና የበአላት አቆጣጠር የቀመረው የቅዱስ ዲሜጥሮስ ታሪክ አንዱ ነው፡፡

ህጋዊና ድንግል የሆነ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ ትውልዱና ነገዱ ግብፅ ሲሆን የተወለደውም በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው እሱ በተወለደበት ዘመን ምዕመናን ያነሱበት አረማውያን የበዙበት ጊዜ ነበር አባቱ አርማስቆስ ይባላል ያባቱ ወንድም ደማስቆስ ይባላል፡፡ ደማስቆስ ልእልት ወይን የምትባል ልጅ ወልዶ ሞተ በሚሞትበትም ጊዜ ልጄ ልእልት ወይን አስራ አምስት ዐመት ሳይሆናት እንዳታጋቧት ብሎ ተናዞ ሞተ አጎቷ የድሜጥሮስ አባት አሳደጋት ከድሜጥሮስም ጋር አንድ ላይ አድገዋል አስራ አምስት ዓመት ሲሆናት ከክርስቲያን ወገን ለሷ የሚሆን ደህና ሰው ቢያጡ ለአሕዛብ አጋብተናት ሃይማኖት ከማፍረስ ተዘምዶተ ስጋ ይፍረስ ብለው ለጎቷ ልጅ ለዲሜጥሮስ አጋቧት፡፡

ዲሜጥሮስ ኑሮው ግብርና ነበርና ከእለታት አንድ ቀን ከተክል ቦታ ሲገባ ያለጊዜው ያፈራች የወይን ዘለላ አገኘ ወስዶ ለሚስቱ ሰጣት እሷም ይህማ መቼ ለኛ ይገባል ለአባታችን ለሊቀ ጳጳሱ ነው እንጂ አለችው አሁንም ወስደህ ከሊቀ ጳጳሱ በረከት ተቀበልበት ብላ በንጹህ ሙዳይ አድርጋ ሰጠችው፡፡ ያን ጊዜ የነበረው ሊቀ ጳጳስ ዮልያና ይባላል አርጅቶ ደክሞ ነበርና ሕዝብ ተሰብስበው አባታችን አንተ ደከምክ እኛን የሚጠብቀን ሰው ስጠን አሉት ፡፡ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመውን እንድናውቅ ሱባኤ እንግባ አላቸው፡፡ ሱባኤ ቢገቡ ለሱ እለቱን ተገልፆለታል፡፡ ሕዝቡም ሱባኤያቸውን ሲጨርሱ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመውን አገኛችሁት አላቸው እኛስ አላገኘነውም አሉት ፡፡ እኔስ አግኝቼዋለሁ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ያለጊዜው ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ የመጣው ነው አላቸው፡፡

ወዲያው ዲሜጥሮስ ወይኑን ይዞ ሄዶ ከበር ቆሞ ንገሩልኝ አለ ግባ በሉት ብሎ እሱን አስገብቶ ያልኳችሁ ሰው ይህ ነው ብሎ ሾሞላቸው እሱ ወዲያው አርፏል፡፡ ሕዝቡም እሱን ቀብረው አባታችን የሰጠን አንተን ነውና ተሾምልን አሉት፡፡ ድንግሉ በሚቀመጥበት ወንበር እኔ ህጋዊ ምሁር በሚቀመጥበት እኔ ጨዋው ጻድቁ በሚቀመጥበት ወንበር እኔ ሃጥኡ መቀመጥ አይገባኝም አይሆንም አላቸው ‹‹ወአዛዎ በኩርህ›› ይላል አባታችን የሰጠን አንተን ነውና ብለው የግድ ይዘው ሾመውታል፡፡ በተሸመም ጊዜ የህዝብ ኃጢአት ተገልፆ እየታየው አንተ በቅተሀል ቁረብ አንተ አልበቃህም አትቁረብ እያለ ይከለክላቸው ነበር፡፡

እነሱም እሱ በማይገባው ከሚስቱ ጋር ተቀምጦ እኛን አንተ በቅተሀል ቁረብ አንተ አልበቃህም አትቁረብ እያለ ይከለክለናል እያሉ በጠላትነት ተነሱበት አነሳሳቸውም በግልፅ ከማርቆስ ወንጌላዊ አንስቶ እስከ ዮልያኖስ ድረስ የተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት አስራ አንድ ናቸው እሱ አስራ ሁለተኛ ነው፡፡

አነሱም ንፁሀን ድንግል ናቸው በትምህርት ብሉይና ሀዲስን የሚያውቁ ምሁራን ናቸው፡፡ ዲሜጥሮስ ግን ትምህርት የሌለው ደሃ ታጥቆ ሞፈር አርቆ ተክል አፅድቆ የሚኖር ገበሬ ነበር፡፡

ከእለታት አንድ ቀን የቀድሞ አባታችን አንቀፀ ብፁአንን አንቀፀ አባግዕን አንብቦ ተርጉሞ ይነግረን ነበር አባታችን አንተም አንቀፀ ብፁአንን አንቀፀ አባግዕን አንብበህ ተርጉመህ ንገረን አሉት፡፡ ይህንንም ማለታቸው ያልተማረ ገበሬ ነው አይሆንለትም በዚህ እንሽረዋለን ብለው የሚሸርቡትን ምክንያት ሲሹነው፡፡ እሱ ግን መንፈስ ቅዱስ ገልፆለት አንብቦ ተርጉሞ ነግሯቸዋል፡፡ ከዚህ አያይዞ ብሉይ ሐዲስ ተገልፆለት ተርጉሞላቸዋል ህዝቡም የሚሽሩበት ምክንያጥ ቢያጡ

መልአኩም ተገልፆ ‹‹ክሥት ሎሙ ክብርከ ከመ ኢትኃጎሉ ሕዝብ በእንቲአብ›› ይላል ‹‹ሕዝቡ አንተን እያሙ በኃጢአት እንዳይጎዱ ክብርህን ግለፅላቸው›› አለው፡፡

እሱም እንጨት አሰብስቦ እሱ ከእንጨቱ ላይ ሆኖ በእሳት አቃጥሉት አላቸው በእሳት አቃጠሉት ሕዝቡም በምን ምክንያት እንሽረዋልን ስንል ከእሳት ገብቶ ሞተልንሳ እያሉ ሲደሰቱ ነበልባሉ ነበልባሉ ከበረደ ፍሙ ከመረተ በኃላ ከእሳቱ መካከል ቆሞ አዮት አለ አልሞተም አሉ አሁንም አላመኑኝ ብሎ ሚስቱን አስጠርቶ ንዒ ስፍሒ አድፍኪ ይላል ፍሙን በእጁ እያፈሰ ነጭ ሀር ለብሳ ነበር ከልብሷ ላይ አድርጎ ሂጂ እየዞርሽ ለሕዝቡ አሳይ አላት እሷም እሳቱን በልብሷ ታቅፋ ከተጋባን አርባ አመታችን ነው በልማደ ብእሲ ወብእሲት አንተዋወቅም በከንቱ አትሙት የንፅህናችን መሰረት ይህ ነው ብላ አስረድታቸዋለች፡፡

እሳት የታቀፈችበት ልብሷን ቢመለከቱ እንኳን ሊቃጠል ጠቆር እንኳ አላለም ሕዝቡም አባታችን ነገሩ ምንድን ነው አስረዳን አልገባንም አሉት እኔና ልእልተ ወይን ከተጋባን አርባ ስምንት አመታችን ነው በአንድ አልጋ ላይ እየተኛን አንድ ምንጣፍ አንጥፈን አንድ ልብስ ለብሰን ስንኖር በልማደ ብእሲ ወብእሲት አንተዋወቅም አላቸው አባታችን ይቅር በለን ብለዋል፡፡ እሱም ይፍታ ይህድግ ብሎ ናዟቸዋል፡፡ ኑዛዜ ያንጊዜ ተጀምሮል፡፡

ሕዝቡ ከዘመን ብዛት የተነሳ ቁጥር ቢፋለስባቸው አብይ ፆምን ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሀሙስ፣ዓርብ፣ ቅዳሜ፣እሁድ ይጀምሩ ነበር፡፡ ሆሳዕናንም እንደዚሁ በማንኛውም ቀን ያውሉ ነበር ስቅለትን እንሳኤንም ጾምን ጾመው ሳይፈስኩ ቆይተው እንደገና መጋቢት 23 ቀን ጀምረው ሰሚነ ህማማትን ይፆሙና መጋቢት 27 ቀን ቅዳሜም እሁድም ቢውል ስቅለትን በዘያ ቀን ያከብሩ ነበር ትንሳኤንም መጋቢት 29 ቀን የሚውልበትን ጠብቀው ያከብሩ ነበር ይህ ሲያያዝ እስከ ዲሜጥሮስ ደረሰ እሱም አብይ ፆም ከሰኞ ደብረ ዘይት ከእሁድስቅለት ከአርብ ትንሳኤ ከእሁድ ርክበ ካህና ከሮብ ዕረገት ከሀሙስ ጰራቅሊጦስ ከእሁድ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ እንዳይለቅ ሲያስብ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ዘወትር ይህንን ስታስብ ትኖራለህ ሱባኤ ግባና ሃሳብህን በተግባር ግለጸው አለው፡፡ ሱባኤ ገብቶ ዘመን መቁጠሪያ የበአላት የአፆማት ማውጫ ባህረ ሃሳ የሚባለው የቁጥር መጽሀፍ ተገልፆለት ላራቱ ሊቃነ ጳጳሳት ፅፎ ልኮላቸዋል፡፡

እነሱም ነገሩ መልካም እንደሆነ አይተው ተቀብለው አስተምረውበታል፡፡ ጥር 11 ጥምቀት አክብረው በማግስቱ አብይ ፆምን ይጀምራሉ፡፡ የካቲት 21 ሳሉ ከጥር 12 እስከ የካቲት 2130 ቀን ይሆናል፡፡ ከዚህ በኃላ ቆይተው ሆሳእናን መጋቢት 22 ቀን ያከብሩና በ25 ሰሞነ ህማማትን ያከብሩ ነበር፡፡ ዲሜጥሮስ ግን አፅዋማትና በአላት ጥንተ ዕለታቸውን ሳይለቁ በጥንቱ እለታቸው እንዲውሉ በመጥቀስና በተወሳካቸው ወስኖ በዘመኑ ለነበሩት ለሮሙ ሊቀ ጳጳሳት ለፍቅጦር ለአንፆኪያው ሊቀ ጳጳስት ለመክሲሞስ ለኢየሩሳሌም ለአጋብዮስ ፅፎ ቢልክላቸው እነሱም ይህ ነገር በመልክቱ ብቻ አይሆንም ባንድነት ተሰብስበን መወሰን አለብን ብለው ህዳር 10 ቀን ጉባኤ አድርገው ባህረ ሀሳብ ለምእመናን ሁሉ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

በአላት የአፅዋማት አከባበር የዘመን አቆጣጠር ቀደም ሲል በነብያትም አለ፡፡ ለምሳሌ ሰብእ ሰንበታት አፅሞው ለሕዝብክ እያለ ቆጥሯል ግን ነቢያት ዘመንን ቢቆጥሩ ከልደተ ክርስቶስ ለመድረስ ነው ዲሜጥሮስ ግን የራቀ አፅዋማትን የተበታተኑ በአላትን ለመሰብሰብ ነው፡፡

ዲሜጥሮስ ማለት መነፅር ማለት ነውነው መነፅር የራስ ጉድፍ የጥርስ እድፍ ያሳያል፡፡ እሱም የራቀ አፃዎማትን ተበተኑ በአላትን ሰብስቦ ያሳየናል መነፅር አለው አንድም ዲሜጥሮስ ማለት መጥቅ/ደውል ማለት ነው፡፡ ደውል በተመታ ጊዜ ሰውን ሁሉ እንዲሰበስብ እሱም አፆማትን በአላትን ሰብስቧልናል፡፡ ስለዚህ መጥቅዕ አለው፡፡

‹‹ እስመ ከመ መጥቅዕ ዘብርት ወዘሀዲን ዘዕድ ወዘእብከን ያስተጋብእ ሰብእ ውእቱኒ ያስተጋብኤ አፅዋማት ወበዓላት ዘኩሉ አመተ ዓለም ›› እንዲል ድሜጥሮስ ሚስት በገባ ጊዜ 15 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ባገባ በ48 ዐመቱ ይህ በህረ ሃሳብ ተገልጦለት ጽፎ አስተምሯል፡፡ ባህር ማለት ዘመን ማለት ነው ሃሳብ ማለት ቁጥር ማለት ነው፡፡ ‹‹ እስመ በመደልው ዓለወ ዓለመ ወበ መስፈርት ሰርሮ ለባህር እንዲል ዕዝራ ሱታኤል አንደኛው ሁለት ምዕራፍ 37 በሹመት 43 ዘመን ቆይቷል መላ ዘመኑ 106 ነው ስለ ታሪኩ ጥቅምት 12ና ህዳር 10መጋቢት 12 ቀን የሚነበበውን ስንክሳር ተመልከት፡፡ የአባታችን የአቡነ ዲሜጥሮስ ፀሎትና ቡራኬው ለሁላችን ይድረስ አሜን!

ወስብሀት ለእግዚአብሔር


 

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro