በዓለ ዕርገት

 
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በዓለ ዕርገት

በሦስትነቱ ጉድለት በሌለበት ጽርሐ አርያሙ በማይጎበኝና በሩጫ በማይደረስበት በፍጥነት ሊገኝ በማይችል፤ በልቡ ትዕቢት ያለበት ያየው ዘንድ ፈቅዶ ወደ በሩ ለመግባት በማያሰለጥን፤ በሚያስደነግጥ የነጎድጓድ ብልጭታ እና በሚያስፈራ የመብረቅ ድምጽ እንዲሸሽ በሚያደርግ በእግዚአብሔር ስም በኢየሩሳሌም ሰማያዊትና ምእመናን እና ምእመናት በሚሰበሰቡበት በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ምስጋና ይገባዋል መቼም መች ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ (መጽሐፈ ምስጢር ዘአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)

ዕርገት፡- ከታች ወደ ላይ መውጣት የሚል ትርጉም ያለው ነው፡፡ የተነገረው ትንቢት የተመሰለው ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን በሰንበተ ክርስቲያን መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቷል፤ ተነሥቶም አርባ ቀን ለሐዋርያት መጽሐፈ ኪዳን አስተምሯል፡፡ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በ፵(40)ኛው “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እም አርያም፤ ከሰማይ ኃይል እስክታገኙ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ብሏቸው እስከ ቢታንያ አውጥቶ እስከ ፓትርያርክነት ያለውን መዓርግ በአንብሮተ እድ ሾሟቸው ዐርጓል፡፡
ጌታችን መድኃታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሥራውን ጨርሶ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ በአብ ቀኝም ተቀመጠ፡፡ በሥጋ እንደ ዐረገ በዓለም ፍጻሜ ይመጣል (የሐዋ.ሥራ ፩፥፮-፲፮ ፤ ፳፬፥ ሉቃ ፶-፶፩፤ ራእ፩፥፯)

•በጌታችን ዕርገት የሚከተሉትን እናስተውላለን
፩ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በመስቀል ላይ የሠራው የመሥዋዕትነት ሥራ ሁሉ ፍጹም ሆነ፡፡(ዕብ ፱፥፩-፲፪)
፪ በሥልጣን በአብ ቀኝ ተቀመጠ፡፡ (ዕብ ፲፥፲፪)
፫ አስቀድሞ እንደ ተናገረ መንፈስ ቅዱስን ልኳል፡፡ (ዮሐ ፲፭፥፳፮)
፬ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለምእመናን አፈሰሰ፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፪፥፴፫)
፭ የቤተ ክርስቲያን ራስ ሆነ፡፡ (ኤፌ ፩፥፲፱-፳፫)
፮ ሕዝቡን ይጠብቃል፡፡ (ሮሜ ፰፥፴፬ ፤ ዕብ ፯፥፳፭ ፤ ፩ኛዮሐ ፪፥፩)
፯ ቦታ ያዘጋጅልናል፡፡ (ዮሐ ፲፬፥፩)
ከአርባ ዝቅ ብሎ ፴፱ ከፍ ብሎ ፵፩ ቀን ያላደረገው አዳም በ፵ ቀን ያጣትን ልጅነት እንደመለሰ ለማጠየቅ ነው፡፡ ማረጉም ከእመቤታችን በነሣው ሥጋ ነው፡፡ ስለምን ቢሉ ተለየ ተለወጠ ላሉት እንዳይመቻቸው አንድም ቅዱሳን ማረጋቸው ገነት መንግሥተ ሰማያት መግባታቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡
ትስብእትን ከመለኮታዊ ኃይል ጋር አንድ ያደርጋት ዘንድ በዕርገቱ ጊዜ እየራቃቸው ሄደ፡፡ ስለ ሰው ልጅ ባለው ፍቅር በምድር ያገኛት የቀደመው መከራ አለፈ ጉስቁልናም ቆመ፤ አሁን ግን በመለኮታዊ ልዕልና ዓርጋ በአብ ቀኝ ተቀመጠች፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ያለመሰላል በፈጣን እና በሚያበራ ደመና ዐረገ መለኮቱ ያፋጥነዋልና ወደ አየርም ተመጠቀ ኪሩቤል የሚባሉ መላእክት ያሳርጉት ዘንድ አልመጡም፤ በመለኮታዊ ኃይሉ ዐርጎ በአብ ቀኝ በእነሱ ላይ ተቀመጠ፡፡
ምንጭ
(መጽሐፈ ምስጢር ዘአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ለዓለመ ዓለም አሜን!

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro