ምኩራብ (፫ኛ ሳምንት)

 

 
ምኩራብ

ወንጌል፡- ዮሐ ፪፥፲፪
‹‹ከዚህም በኃላ እርሱ፣ እናቱ፣ ወንድሞቹ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም ወርደው በዚያ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ ብዙም አይደለም የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በምኩራብም ላሙን፣ በጉን፣ ርግቡን የሚሸጡትን የሚገዙትንም አገኘ፤ ለዋጮችንም ተቀምጠው ከገመድ የተሰራ አለንጋ አበጀ በጉንም ላሙንም ሁሉንም ከምኩራብ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ወርቅ በተነ፤ መደርደሪያቸውንም አፈረሰ፤ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፤ ርግብ ሻጮችንም ይህን ከዚህ አውጡ፤ ወዲያ በሉ የአባቴን ቤት የገበያ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱ የቤትህ ቅናት በላኝ የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ አሰቡ፡፡ አይሁድም መልሰው ይህን የምታደርገው ምን ምልክት ታሳያለህ አሉት፤ጌታ ኢየሱስም ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሶስተኛውም ቀን አነሳዋለሁ ብሎ መለሰላቸው፡፡ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ በዐርባ ስድስት ዓመት ተሰራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሳዋለህን? አሉት፡፡ እርሱ ግን ቤት ስለተባለ ስለ ስጋው ነገራቸው ፤ ከሙታን በተነሳ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደነገራቸው አሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃል ጌታ ኢየሱስ በነገራቸው ነገርም አመኑ፡፡ ጌታ ኢየሱስም በበዓለ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ አመኑበት፤ እሱ ጌታ ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና፡፡የሰውንም ሥራውን ሊነግሩት አይሻም፤ሰውን እሱ ራሱ ያውቀዋልና፡፡››
ዋናው መልዕክት፡-
• በቤተ እግዚአብሔር ያልሆነ ስራ ሲሰሩ መቆርቆር ተገቢ ነው፡፡
• በቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ሥጋዊ ገበያ ማቆም ታላቅ ነውር ነው፡፡
• ሰው ለጊዜው የማይሆነውን ቢሆን እግዚአብሔር ፍጻሜውን ያውቀዋል፡፡
ተጨማሪ መልዕክት
• ጌታችን ሥልጣነ ክህነትን ገንዘብ አድርጎ ክፉውን ሁሉ እንዳስወገደ ካህናት በሥልጣነ ክህነታቸው በሰው ያለውን ክፉ መንፈስ ሊያስወግዱ ደዌያትን ሁሉ ሲፈውሱ ይገባቸዋል፡፡
‹‹ድውያንን ፈውሱ›› ሉቃ ፲፥፱፣ያዕ ፭፥፲፬
• /መዝሙር ዘምኩራብ ቦአ ኢየሱስ ምኩራብ አይሁድ/
ቁላ. ፪፥፲፮
ያዕ. ፪፥፲፬
ዮሐ. ሥ ፲፥፩‐፱
ምስባክ፡- መዝ ፷፰፥፱
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ
ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ

ትርጉም፡-
የቤትህ ቅንዐት በልቶኛልና፡፡
የሚገዳደሩህ ሰዎች ስድባቸው በላዬ ወድቋል፡፡
ነፍሴንም( ሰውነቴን) በጾም ቀጣኋት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ለዓለመ ዓለም አሜን!!!
ምንጭ
ምስባክ ቃለ ሕይወት ሊቀ ጽጉሃን ኄለ ጊዮርጊስ ዳኘ
ሰባቱ አጽዋማት ተስፋዬ ምትኩ

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro