ሕንጸተ ቤታ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ሠኔ ፳ በዚኽች ቀን “ሕንጸተ ቤታ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም” እመቤታችን በዐረገች በ፬ዓመት ጳውሎስና በርናባስ ፊልጵስዩስ ገብተው አስተማሩ፤ሕዝቡም አምነው ተጠመቁ እንግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሒዱ አሏቸው የለመድነውን ከከለከላችሁንማ መካነ ጸሎት ስጡን አሏቸው፡፡ እንዲህ ብንላቸው እንዲህ አሉን ብለው ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስ ላኩ አልቦ ‹‹ዘትገብሩ ወኢምንተኒ ዘእንበለ ትእዛዙ ወምክሩ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ›› ያለጌታችን ፈቃድ አንዳች ልታደርጉ አይገባም እናንተም ጸልዩ እኛም እንጸልያለን ብለው ላኩባቸው፡፡ ሱባዔ ሲጨርሱ በዚህ ዕለት ጌታ በሩቅም በቅርብም ያሉ ደቀመዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው፡፡ ዮሐንስ ጌታዬ ለምን ሰበሰብከን ብሎ ጠየቀ ጌታም በእናቴ ስም ጽንፍ እስከ ጽንፍ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንጻ ቤተክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ነው አለው፡፡ ይህንን ብሎ ወደ ምሥራቅ ወሰዳቸው ተራርቀው የነበሩ ፫ ደንጊያዎች ነበሩ፡፡ በተአምራት አቀራርቦ ቁመቱን ወርዱን መጥኖ ሠጣቸው ‹‹ወአዕባንኒ ይለመልሙ በእዴሆሙ›› ይላል እሳት እንዳየው ሰም ከእጃቸው እየለመለሙ /እየተሳቡ/ ቁመቱን ፳፬ ወርዱን ፲፪ ክንድ አድርገው ሠርተውታል፡፡ ‹‹ወይእዜኒ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ›› እንግዲህ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ ብሏቸው ዐረገ፡፡ በማግሥቱ ሰኔ ፳፩ ቀን እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ዳግመኛም ጴጥሮስን እጁን ጭኖ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል፡፡ በዚህም ጊዜ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ሐዋርያት አንድ ሆነው አመስግነዋል፡፡ የእናታችን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት ከሁላችን ጋር ይኑር፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡-  ተዓምረ ማርያም እና መዝገበ ታሪክ ክፍል ፪

                     ©2017.Temro Mastemar - All Rights Reserved. Website by Temro